አላቅሱን!

               መቼም የዋሽንግተን ዲሲው ደብረሃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተከርስቲያን ጉዳይ ተወርቶ የሚያልቅ አልሆነም፡፡ አንዱን ሲይዙት ሌላ ጅራት ያወጣል፡፡ ባለፈው ለንባብ ባቀረብኩላችሁ “እውነትን ሰቀሏት” በሚለው ጽሁፍ ላይ በታህሳስ ቅዱስ ገብርኤል ሥርዓተ ንግስ ላይ ታቦት ከመውጣቱ ቀደም ብሎ ምዕመናን ለዓመታት በደከሙበት፣ ጉልበታቸውንም ሆነ ግዜያቸውን  ጭምር የከሰከሱበት ቤተክርስቲያን ከክርስቲያናዊ እምነት ውጭ በአጉል መሪዎች አግድም እየተመራ በክህደት ቁልቁለት ሽምጥ እየጋለበ መሆኑን ለማሳወቅና ከተቻለም የተሻለ አቅጣጫ ለማስቀየስ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ወርቃማ ዕድል ገጥሟቸው ነበር፡፡

                 ምዕመናን በዕለቱ ተገኝተው ለነበሩት ትልቅ እንግዳችን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ፣ ደርጉ/ቦርዱ የፈጸመውን በድብቅ የሰባኬ ወንጌሉን የክህነት ሹመት መከልከልና ከሥራ መታገድ ምክንያት እንዲገለጽላቸው ተማፅነዋል፡፡ እርምጃው የቅስና ሰጪውን ሊቀጳጳስ ሥልጣንም ጭምር በእብሪት የተጋፋና የምዕመኑንም የበላይነት እንደዋዛ ያየ አምባገነንነት እየሰፈነ መሆኑንም ያስተጋባ በዕለቱ በቦታው ለነበረውም ሆነ ለሰማው ሁሉ ግልጽ ሆኖ ታየ፡፡ ዲያቆናቱም  የወንድማቸውን የሰባኬ ወንጌሉን ከሥራ መታገድ አስመልክቶ የሥርአቱ መጣስ ለውደፊቱ ሊያመጣ የሚችለው ቀውስ ከወዲሁ ስለታያቸው እጃቸውን ታጥበው ከደሙ ንጹህ ነን ብለው ዕለቱን በየቤታቸው ማሳለፉን መርጠው ነበር፡፡

           ጉዳዩን ካለፈው ጋር ላያይዝላችሁ ብዬ እንጂ ላወጋችሁ ያሰብኩት እንኳን ሌላ ነው፡፡ በተሳካ ሆኔታ የተከናወነው ተቃውሞ ከጎሮዶማኖቹ አኳያ እንዴት እንደተገመገመ ላሳያችሁ ነው የተነሳሁት፡፡ መቼም ያ ዘረኛ ቡድንና ጭራዎቹ በጣም የሚፈሩትና የሚጠሉት ጉዳይ የሥራችውን ገሃድ መውጣት እንድሆነ ለናንተ አልነግራችሁም፡፡ ሥራቸው ጨለማን ተገን አድርጎ፣ እያደባ የሚሽሎከለክ፣ ሸምቆ የሚያጠቃ፣ ተደብቆ የሚነጥቅ፣ የምዕመንን ገንዘቡንና ስሙን  እንደ ሥጋ የሚቦጭቅ በመሆኑ የዕኩይ ሥራቸው ለሕዝብ መገለጥ እስከ ገሀነም ድረስ ያስበረግጋቸውል፡፡ መቼም ትውውቅ የሚኖራቸው ያው ከገሃነም ጋር ነው ብዬ ነው፡፡ የገነት መንገድማ ጉዞውን በግልጽ፣ በብርሃን፣ በፀሐይ፣ ለሚያደርግ አማኝ ነው፡፡

           ትልቁ ጥያቄያቸው፣ ምነው ሌላ ግዜ ከቅዱስ ገብርኤል ንግስ ቀን ውጭ ቢያደርጉት? ሕዝበ ክርስቲያን ከየእስቴቱ በተሰበሰበበት፣ የአገር ሁሉ እይታ እኛ ላይ በሆነበት ዕለት እኩይ ድርጊታችንን አደባባይ አወጡብን ነው ቁጭታቸው፡፡ ምነው እርስበራሳቸን ብንነጋገርበት ሁሉ ብለዋል አሉ፡፡ እውን እነሱ ለመልካም ምግባር ሊቆሙ? በሰላም ለሰላም ሊወያዩ? ምነው ምርጫው የተካሄ ሰሞን አሸናፊ ፓርቲ ነንና ያሰኘንን እናደርጋለን፣ ፕሮግራማችንን እናስፈጽማለን ሲሉ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ስለ ሰላም አወሩ? ምዕመኑ የት ይደርሳል፣ ምን ሊያመጣ ያሉቱ ናቸው ወይስ የነሱን ተንኮል በሹልክታ የሚያራምዱላቸው በእግራቸው ሌሎችን መለመሉ? ፕሮግራማችንን እናስፈጽማለን ያሉትስ የትኛውን ፕሮግራም ነበር? ይሄን የወንጌል መምህሩንና ዲያቆናቱን ያባረሩበትን ፕሮግራም ነው ወይስ ሊቀጳጳሱን ለማባረር የሚያቅራሩበትን ነው? በምዕመኑ ላይ ጦር የሚሰብቁበትም አንዱ ፕሮግራማቸው ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ፡፡ የሚሰብቁትን ጦር ግን መቼ እንደሚወርውሩት ስለማይታወቅ ምዕመን ከወዲሁ ሊዘጋጅበት ይገባል፤ ያላወቁ አለቁ ነውና ነገሩ፡፡ ዲቁናውን፣ ቅስናውን፣ መምህርነቱንና ጵጵስናውንማ በሱዳን ሻይ ቤቶች ተሹመውት ሊሆን ስለሚችል በቤተክርስቲያኑን የመንፈሳዊ ሥራውን ማካሄድ እንኳን ብዙም አይገዳቸውም፡፡ ለካ ፈረንጅ ትንሽ እውቀት አደገኛ ነው የሚለው እውነቱን ኖሯል!

           ሁለተኛው ጥያቄያቸው የገንዘብ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ቅዱስ ገብርኤልን ብሎ ከሚመጣው አማኝ ሕዝብ ገንዘብ በገፍ በአካፋ ለማጋበስ የተዘጋጁበት ቀን ነበር፡፡ የገንዘብ ነገር መቼም ሞታቸው ነው፡፡ በሙዳየ ምጽዋት መድረቅ ጉዳይማ ሲበሳጩ፣ ሲቆናጠሩ፣ በአውደ ምህረት ላይ ሲሳደቡ፣ አንዴ ውቃቢ አለባችሁ አንዴ በጥሩ ቤት ውስጥ ኖራችሁ እያሉ ሲሳለቁብን ሰነበቱ፡፡ ገንዘባችንን ከኪሳችን የማውለቅ ያህል ወረዱብን፡፡ አስፈራሩነ! ይሄን ሲሉ ጭራሽ ዋናው ገንዘብ መሰብሰቢያው ቀን ላይ ያላሰቡት ዱብዳ ገጠማቸው፡፡ ምዕመንን ለማስፈራሪያ ያቆሙት የፖሊስ መኪናም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አልረባቸውም፤ እርግጥ የመበራቱ መብለጭለጭ ለበዓሉ ድምቀት ይሰጠዋል ብለው ካልሆነ በስተቀር፡፡ ግራ በመጋባት እራሳቸውን ሲያኩ የዋሉበት ቀን ሆነ፡፡

             በዚህ ሁሉ ላይ እንግዲህ ሰዉን ሁሉ አንድ በአንድ ሲያወግዙ ሲሳደቡ ሲተናኮሉ አንድም ግዜ እራሳቸውን  አንድ ትልቅ ጥያቄ ጠይቀው የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ እኛ የት ላይ ተሳሳትን? ምን አጠፋን? ምዕመን ለምን አንቅሮ ተፋን? የሚል ጥያቄ  በመካከላቸው አንስተው ተወያይተዋል የሚል ግምት በፍጽም የለኝም፡፡ ምን አጥፍቼ ይሆን፣ ምን በድዬ፣ የት ላይ ተሳሳቼ ይሆን የሚል እራሱ የከበደው የጨዋ፣ የትሁት፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት/ያደረባቸው ህሊና ያላቸው ሰዎች አካሄድ ነው፡፡ የለም፣ ረጋ በሉ፣ የያዝነው መንገድ የጥፋት መንገድ ነው ብሎ የሚመክር፣ የሚገስጽ አዕምሮ ያለው እመሃላቸው ባለመኖሩ ተያይዘው፣ ቤተክርስቲያኑንም አጥፍተው ሊጠፉ የጥፋት አፋፍ ላይ ቆመዋል፡፡ መንገዳችን እየቅል ስለሆነ፣ ቤተክርስቲያን የሚመጡበትን ዋናውን ምክንያት በትክክል ማስቀመጥ ተሳነን እንጂ፣ እግዚአብሔርን ለማምለክ እንዳልሆነ ግን ለረዥም ዓመታት አካሄዳቸውን የተከታተልነው ቀርቶ ሌላውም ይገነዘበዋል ባይ ነኝ፡፡ የሚያሳዝነው ሁኔታ ቦርዱም የነሱን ዓይነት ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ለነገሩ እነሱ ከፈጠሩት ቦርድስ ምን ሊጠበቅ ይችላል? አመኔታው ጉባኤስ ቢሆን በየቦታው እየዞረ የሰው ስም ከመለቅለቅና አውደምሕረት ላይ ቆሞ ምዕመንን ከመዝለፍ  ሌላ ምን ጥሩ ነገር ታየበት? ማንን አስታረቀ? ማንን አስማማ? እየዞረ የሰው ሥጋ የሚበላው ይሄው ከራሱ የተጣላ አመኔታ ጉባኤ አይደለም?

           የንግሱ ዕለት ነገሩ የተበላሸብኝ፣ ለኔ ማለቴ ነው፣ ገና ወደ ቤተክርስቲያኑ ልገባ ደረጃውን ስወጣ ነበር፡፡ ያለቦርዱ ፍቃድ ፎቶግራፍ፣ ቪዲዮ ምናምን ማንሳት ክልክል መሆኑን ያበሰረችዋ ማስታወቂያ የነበረኝን ጥሩ መንፈስ ሰረቀችብኝ፡፡ ቤተክርስቲያን የጦር ካምፕ አይደል፣ ሚስጥራዊ የምርምርና ሥርጸት ማዕከል አይደል፣ ምዕምኑ ላይ በገዛ ቤቱ የዚህ ዐይነት ማዕቀብ መጣል በነሱ ቤት እግዚአብሔር የሚወደው ደግ ሥራ መሆኑ ይሆን?  ምናልባት በሻለቃ መልከፄዴቅ የሚመራው የስም አይጠሬ ወረዳ ኮማንዶ ጦር ነጋ አልነጋ ብሎ ምድር ሰማዩ ሳይላቀቅ ቤተክርስቲያኑን ሊያጠቃ ከሚችለው ከሱዳን ጦር ለመከላከል መቅደስ ውስጥ መሽጎ ይሆን? ማን ያውቃል! የእግዚአብሔር መንገድ እስካሁን ካልገባቸው ደግሞ ካሁን በኋላስ ይዋጥላቸዋል ብላችሁ ነው? ብቻ ለማንኛውም እኔም አዲሰ ትምህርት ቀሰምኩ፤ እነሱ ከሻይ ቤቱ ውስጥ ወጡ ማለት ሻይ ቤቱ ከነሱ ውስጥ ወጣ ማለት እንዳልሆነ ዘግይቼ ተረዳሁት፡፡

           ታዲያ የዛችን አሳዛኝ ማስጠንቀቂያ ይዘት በትካዜ ሳውጠነጥን መኪና ማቆሚያው አካባቢ የነበረው ከወትሮው ሞቅ ያለ ግርግር ትኩረቴን ሳበው፡፡ ለመኪና ፓርኪንግ ዕርዳታ የተሰለፉት ሰዎች በብዛት ከዚህ በፊት አይቻቸው የማላውቅ አዳዲሶች መሆናቸውን ተመለከትኩ፡፡ በሌላው አቅጣጫ ደግሞ በአንድ ቫን ሞልተው የተቀመጡ ሰዎችን ስመለከት ከሌላው ግዜ የንግሥ በዓል የተለየ ምን ጉዳይ ተፈጥሮ ይሆን ብዬ በልቤ ሥጋት አደረብኝ፡፡ ወደ ውስጥ ስገባ ኮሪዶሩን ግራና ቀኝ የተኮለኮሉትን የወትሮዎቹን መንደር አባጮች ስመለከት ውጭ የቆመው ቡጭቅጫቂ ጦር የነሱ የይድረስ ምልምል ሚሊሽያ መሆኑን ያለምንም ጥርጥር አውቅኩት፡፡ ግን ለምን ተጨማሪ ሃይል አስፈለጋቸው? ምዕመናን እኮ ቤተክርስቲያን የሚመጡት እግዚአብሄርን ለማምለክ እንጂ እንደነሱ ለውጊያ ወይም ለዕኩይ ተግባር በፍጹም አይደለም፡፡ በሠላም እናምልክበት እንጂ ከክትፎው ከጥብሱ ከምትበሉት አካፍሉን አላሉም፡፡ እሱን ለናንተም ባረጋላችሁ፡፡

           እነዚህን የበጥባጭ ጦር አባላት ምዕመን በሙሉ ማንነታቸውን በውል አውቆታል፡፡ እውነቱን ለመናገር ባለፈው ምርጫ ካከናወኑት የሸፍጥ ሥራ በኋላ ቤቱ ውስጥ ጉዳቸውን የሚያውቅ በሙሉ ዐይኑ እያየ ጆሮው እየሰማ ወድቃችሁ ተነሱ የሚላቸው ማንም የለም፡፡ ቡድናቸው እንግዲህ በቀጥታ በቦሌ ሳይሆን ለማስመሰል በሽንጥ በጅቡቲ ወይም በናይሮቢ አዲስ አበባ ገብተው መሬት ተቀብለው በማህበር ቤት በመሥራት ላይ ያሉ፣ የዕድር ገንዘብ ወደግል ኤቲኤምነት የቀየሩ፣ የታክሲ ማህበራትን በክስ የሚያምሱ፣ ሕጋዊነት የሌለው የሲኖዶስ ድጋፍ ሰጪ ግብረሃይል አባል ነን ብለው በተላላኪነታቸ የሚኮሩ ከንቱዎች ናቸው፡፡ በቀላማጅነት ተኮንኖ ጎንደር ከተማ መሀል ጀርባውንና መቀመጫውን  እንደ ህፃን ልጅ ተገርፎ ባደባባይ ተደፍቶ ይቅርታ የጠየቀውም እንዳለበት እናውቃለን፡፡ በአዲስ አበባና በጎንደር ገስጋሽ የቀይ ሽብር ተዋናዮችንም ያቀፈ መሆኑ የሁሉም ሚስጥር ሆኗል፡፡

           ይህ ቡድን ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ ለተከታታይ ሳምንታት ከሰባ ስምንት ግዜያት በላይ በተለያዩ ቦታዎች እየተሰባሰበ፣ እወደድ ባይ አባላትን በአስመራጭ ኮሚቴ አባልነት ምርጫውን ያለ ምንም ይሉኝታ ወደ ፈለጉት አቅጣጫ እንዲመሩላቸው ሲሰይሙ፣ ተመራጮችንም እዚያው ተከታታይ ስብሰባዎቻችው ላይ ወስነው የሥራ ድርሻቸውንም አደላድለው የመጨረሳቸው ዜና ያኔውኑ ነበር የደረሰን፡፡ ይህ ድርጅታዊ አሠራር ከእንደነሱ ዓይነት ሞራለ ልል ግለሰቦች የምንጠብቀው ቢሆንም እንዲያው ምናልባት የያዘቸው አባዜ ገለል ብሎላቸው እንደሆን የሚል ትንሽ ተስፋ አለመቁረጥ በምዕመኑ ዘንድ አድሮ ነበር፡፡  የለንደኑም ጳጳስ ለተወሰኑ ግዜያት በዚሁ ባልተቀደሰ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ሆነው እንደነበርም ሰበር ዜና በግዜው ደረሰን፡፡ ታዲያ ሰባ ስምንት ግዜ መግተልተል ያሰፈለጋቸው እነዚህን ድኩማን ለመምረጥ ነበር? ሥልጣኑን የፈለጉት በደካሞች ተንተርሰው ኤኮኖሚያዊና ጎጣዊ መርሀግብራቸውን ለማስፈጸም ከሆነ ካለፈው ያፍዝ ያደንግዝ አገዛዝ ብዙ ተምረናልና ምላሹ ቀላል ይሆናል ብለው እንዳያስቡ፡፡

           ስደተኞች ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞቼ፣ እንግዲህ በዚች በአሁኗ ወቅት መንታ መንገድ ላይ ደርሰናል፡፡ መንግዶቹ  አንዱ ወደ ጥፋት ሌላው ወደ መዳን የሚወስዱ ናቸው፡፡ እኛ የስደተኛው ሲኖዶሰ ተከታይ የሆነው ሕጋዊ የሃይማኖታቸን ተወካይ መሆኑን በርግጥ ስለምናምንበት ነው፡፡ አለኝታችን ብለን የምናምንበት ስደተኛው ሲኖዶሳችን ልጅነቱን እንኳን ሳይጨርስ በዐይናችን እያየነው በህቅ እንቅ እየቃተተ ወደ ህልፈት በማዝገም ላይ ይገኛል፡፡ የግሌ ሲኖዶስ ነውና እኔ እንደፈለግኩት  በጭንቅላቱ ካላስኬድኩት አፈርሰዋለሁ አስፈርሰዋለሁ ብለው ቤቱን ሊበትኑት ቆርጠው የተነሱት የጦሩ ሰው ሻለቃ መልከፄዴቅ ናቸው፡፡ እያንዳንዱን ቤተክርስቲያን እየዞሩ ማበጡን ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ ሁሉም ቦታ ላይ ሲበጠብጡ ቦርዱን አቅፈው ሕዝቡን ገፍተው ነው፡፡

           ዴንቨርን፣ ሲያትልን፣ ሳንዲዬጎን፣ ኦክላንድን የማይጠፋ እሳት የማይበርድ ጥላቻ ለኩሰውበታል፡፡ ዋሽንግተን ዲሲን ደሞ ሕዝቡን በጎጥ ከፋፍለው፣ በክፍለሀገር ሳይሆን በመንደር፣ ለመናከስ አብቅተውታል፡፡ ምዕመን በዐይኑ ሊያየው የማይፈልገውን የድሮውን ሊቀመንበር ዘመድና ጉዳይ አስፈጻሚ መሪጌታ ከሀገረስብከቱ ኃላፊ እውቅናና ከቅዱስ ከፓትርያርኩ አዎንታ ውጭ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አድርገው ሹመዋል፡፡ ምዕራብ ባሕር ዳርቻ (ዌስት ኮስት) ካለው ሀገረ ስብከታቸው ተነስተው አያገባቸው ገብተው፣ ምሥራቅ ባሕር ዳርቻ (ኢስት ኮስት) በሌላ ሊቀጳጳስ ሀገረስብከት ውስጥ በአምባገነንነት ሹመት ሰጡ፡፡ እውን ይሄ አምባገነንነት ከእግዚአብሕር ነው ትላላችሁ? አሁንማ እሳቸውን እንደእግዚአብሔር የሚያመልክ ግልብጥ የባሃዪ እምነት ተከታይ  አማቻቸው የሊቀመንበርነቱን  ቦታ ስለያዘላቸው ሜዳውም ፈረሱም በጃቸው ገባ፡፡ ከክፉዎች መንገድ እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡ እኒህን ጎጠኛ የጥፋት መልዕክተኛ ከጥፋት መንገዳቸው ባስቸኳይ የሚመልሳቸው ካልተገኘ ባጭር ግዜ ውስጥ የሲኖዶሱ ሥርዓተ ቀብር ላይ እንደምንቆም በርግጠኝነት እነግራችኋለሁ! የፊታችን ዓርብ ደሞ ወደ አውስትራሊያ ሊያቀኑ ነው ተብሏል፡፡ መከረኛ አባ ወልደትንሳኤ አያልነህ ስንት ደክመው፣ ወጥተው ወርደው፣ የስንቱን ፊት አይተው በስንት ዓመት የሰበሰቡትን ሕዝበ ክርስቲያን ባንድ ጀምበር ሊበትኑት ሊያፈርሱባቸ ነው፡፡ ማፍረስ የለመደ እርካታውን የሚያገኘው ከማፍረስ ስለሆነ ከሳቸው ጉዞ በጎ አይጠበቅም፡፡ ቤተክርስቲያናችንን እግዚአብሔር ከአጥፊዎች ይጠብቅልን፡፡

                 ሰው ትክክለኛ ባሕሪው የሚታወቀው በፈተና ወቅት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ፈተና ታዲያ በመከራ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሃብትም ሥልጣንም ለሰው ፈተናዎች ናቸው፡፡ ምንም ከሰውየው ጋር ቅርብ ግንኙነት ባይኖረኝም፣ የሰበካ ጉባኤ ሊቀመንበራችን ምን ያህል ትህትናቸው የተደነቀላቸው የተወራላቸው እንደነበሩ ግን አውቃለሁ፡፡ ያ እውነት ከነበረም አሁን ደግሞ የሚሳዩን ግልባጩን መሆኑ ነው፡፡ እቺም ሥልጣን ሆና ከመቼው ልባቸውን እንዳሳበጠችው ሳስበው ያስደንግጣኛል፡፡ አውደምህረት ላይ ቆመው ወሬኛ ናችሁ ለማለት፣ ገደብ-የለሽ የስልክ ኮንትራታችሁን (አንሊሚትድ) ቀንሱት ሲሉን በጥፊ የመቱኝን ያህል ማመን ተሳነኝ፡፡ ክሳቸው አፍ የወጣም አልመሰለኝ፡፡ ዕብሪት ክሥልጣን ጋር ተደርቦ ይመጣል የሚሉትን ነገር እውነትነት አስመሰከሩ፡፡

                 በወሽመጥ የተተከለ የመልከፄዴቅ ሹመኛ አስተዳደሪ ተብዬ መሪጌታም ቢሆኑ በሚያሳዝን፣ እስከወዲያኛው ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ በትናንትናው ሰንበት ዕለት አውደምህረት ላይ ቆመው በቤተክርሰቲያኑ ውስጥ ቪዲዮ ካሜራ የመጠመዱን ፀረ-ክርስቲያናዊ ዜና በታላቅ ምጸት አበሰሩልን፡፡ ተጠንቀቁ፣ ልብ በሉ እንቅስቃሴያችሁን በሙሉ፣ የምታደርጉትንና የምታውሩትን ሁሉ እንቆጣጠራለን እናዳምጣለን ነበር ያሉን፡፡ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ የዘላበዱትን ሁሉ እኛም በሞባይል ስልክ አስቀርተነዋል፡፡ ለመሆኑ መቅደስ ውስጥም ቪዲዮ አስገቡ ማለት ነው? እነዚህ ሰዎች ያለንበት አገር በምስለኔ የሚተዳደር ይመስላቸው ይሆን? ያለንበት አገር እንጂ መንደር እኮ አይደለም! ሕገመንግስት እኮ አለው! የሀገሪቱን ሕግ እስካልጣሱ ድረስ ዋይት ሃውስ፣ ኮንግሬስ ውስጥ መጮህ መቃወም መቻሉን አልሰሙም ማለት ነው? ፕሬዚዳንቱን መሳደብም ጭምር እንደሚቻል አያውቁም? ኧረ ከማን ጋር ነው እየተነጋገርን ያለነው እባካችሁ? ለመሆኑ ብንነጋገር ምን ሊያደርጉን፣ ምን ሊያስደርጉን ይሆን? ኧረ በባዲራው!

           የራሳቸውን ሳይወጡ ለሌላው ካህን ለመሆን ባልተንጠራሩ! ፉከራቸውን ወደጎን አድርገው በመጀመሪያ ቤተክርስቲያን ታይተው የማያውቁ አራት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ለቤተክርስቲያን ባበቁ! ወይስ እምነታቸው የኖሩበት አገር የይሁዲ ነው? ክርስቶስ ገና ይወለዳል ብለው ይጠብቃሉ ማለት ነው፡፡ ይቅር ይበላቸው!

           እንግዲህ ወንድሞቼ፣ እህቶቼ፣ እናቶቼና አባቶቼ፣ ካካባቢው ለሥራ ጉዳይ ወጣ ስለምል ከሥራዬ በቀር ለሌላ ብዙም ግዜ አላገኝምና ለትንሽ ግዜ እለያችኋለሁ፡፡ ፋታ ካገኘሁም በተቻለኝ መጠን ጆሮዬን አስልቼ አዲስ ጉዳዮችን ለማዳመጥ እሞክራለሁ፡፡ ለክፉውም ለደጉም (ደግ ባይኖርም) እራሳችሁን ጠብቁ፡፡ በሠላም ቆዩኝ፡፡

 ወስብሃት ለእግዚአብሔር

 ወንድማችሁ ኃይለ ገብርኤል ታደገ

About these ads
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

One Response to አላቅሱን!

  1. በፍቅር says:

    አዬ የእኛ ነገር የካሳው መጠን ከበደን መሰለኝ የቅርብ ጊዜው የቀይ ሽብር ሰቆቃ በቀላሉ ተረስቶ ሲኖዶሱንና ደብራችንን እንዲያው እንደዋዛ ለ”ጓዶች” ማስረከባችን በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም ድርብ የሚያስጠይቀን መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ቤተክርስቲያንና ኮሙኒዝም አብረው አይሄዱም፡፡ የከፋፍለህ ግዛው ስውር ደባ ሰለባ ሳንሆን በአስቸኳይ ከደርጋዊው/ኮሙኒስት “ቦርድ/ጓዶች” አስተዳደር ፤ እንዲሁም ሲኖዶሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በ”ሰላም ድርድር” ሰበብ ለአዲስ አበባው ዘመነኞች አሳልፎ ከመስጠት ሴራ ለማዳን በአንድነት እንሥራ፡፡ ክእግዜር የተደበቀ ጉዳይ ሊኖር አይችልም፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Connecting to %s