ከቅኝ አገዛዝ ስር የወጡ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተለይ በአዲስነታችው ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸው እንደነበር ካነበብነውና ከሰማነው ግንዛቤ ሳንወስድ የቀረን አይመስልኝም፡፡ ቅኝ ገዢ አገር ለቆ ሲወጣ ያለ ምንም ተጠያቂነትና ያለምንም ጠያቂ ሲፈልጠው ሲቆርጠውና ሲግጠው የኖረውን አገር ሕዝብ እርስበርሱ እንዲባላ፣ ከጎረቤቱ እንዲናጭና ከቶም ሠላም እንዳይኖረው የማይጠፋ የማይስለመለም የመርዝ እሳት ለኩሶ አንቦግቡጎ ነበር የሚሰናበተው፡፡ ከዚያ በኋላማ ሰው ከጎረቤቱ፣ ወንድም ከወንድሙ፣ ከእህቱ፣ አንድ ዘር ከሌላው ዘር፣ ኩታ ገጠም አገሮች እርስ በርሳቸው መናከስ ነው፡፡ የሚንቦገቦገውን እሳት ያራግቡታል፡፡ የቅኝ ገዢ በግዛቱ ላይ እያለ ያገር ተወላጅ የውስጥ አጋር ባንዶች ከመሶቡ ላይ ትራፊውን እየተቀራመዱ የሚደልቡ ሁሉ ለቆ ሲወጣም የሥልጣን ኮርቻ ላይ ፊጥ ይላሉ፡፡ እነሆድ አምላኩ ትልቁ ምኞታቸው ባኗኗራቸው ለቆ የሄደውን ፈረንጅ ጌታቸውን መምሰል ነው፡፡
ቅኝ ገዢ ሕዝብን አባልቶ የሚሄደው የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ነበር፡፡ ሥልጣን በያዙት የድሮ አሽከሮቹ አቅራቢነት ጥሬ ዕቃ በርካሽ ያገኛል፣ በሥልጣን ላይ በነበረበት ግዜ የሠራቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሎችና ዝርፊያዎች ይደበቁለታል፤ ባጭሩ የእጅ ኦዙር ቅኝ አገዛዝ ይሰፍናል፣ ይንሠራፋል፡፡ በውጭ ጨፍጫፊ ቦታ አገር በቀል ጨፍጫፊ ይተካል፣ ምስኪኑ ሕዝብ ግን በገባርነቱ እንዲቀጥል ይጠበቅበታል፣ ይበረታታል፡፡ አለበለዚያ ግን ይታፈናል ይታሠራል!
ቀደም ሲል ለረዥም ዓመታት ልክ እንደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በኣንድ ግለሰብ ይመራ የነበረው የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በአሁኑ ወቅት በዐይናችን እያየነው በፍጥነት የፖለቲካ ድርጅትነት ካባም ለመደረብ በቅቷል፡፡ በእውቅ በቀድሞው ሊቀመንበር ታማኝነታችው ተመስክሮላቸው የተመለመሉት አዲሶቹ የአመራር አባላትም፣ ጌታቸው ገነዘብንም ሆነ ንብረትን ጨምሮ ለምንም ነገር ተጠያቂነት እንዳይመጣባቸው በጽኑ እየታገሉላቸው ነው፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ታዲያ እውን እዚያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰው ታጣና ነው እቀድሞው ቦርድ ውስጥ በእውቅ ተመልምለው እንዲገቡ ተደርገው የነበሩት ሁለት የቦርድ አባላት እንደገና አዲሱ ቦርድ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉት? ለምን ተፈለጉ፣ ባላቸው ከፍተኛ የሥራ ልምድና ከፍተኛ እውቀት፣ ታማኝነት ወይስ ታዛዥነት? አሁን የቦርዱ ጸሀፊ የሆኑትስ ቢሆኑ በቀድው ሊቀመንበር የትምህርት ኮሚቴ መሪነት የተሾሙት አይደሉም? የተፈለጉትስ በቅድሞው ሊቀመንበር ቤተሰብ “መልቲካልቸራል ዩዝ ዴቬሎፕሜንት ኢንኮርፖሬትድ” በመባል የሚታወቀውን ከመንግስት ዳጎስ ያለ ገቢ በእርዳታ የሚያስገኘውን የሰመር ካምፕ ፕሮግራም ቀጣይነት ለማስረገጥ፣ ከምዕመን የተሰወረ ገቢውም በስውር እንዲቀጥል አይደለም? ፎቶግራፍ እየተነሱ እርዳታ የሚለመንባቸው ኅፃናትስ ቢሆኑ የምዕመናን ልጆች አይደሉም? ምዕመናን ልጆቻቸውን ቤተክርስቲያን የሚያመጡት እኮ ቤተክርስቲያን እየለመዱ እንዲያድጉላቸው እንጂ እንዲለመንባቸው አልነበረም፡፡ ምክትል ሊቀመንበሩስ ቢሆኑ እውነት ይሁንም ሀስት በአሁኑ ጊዜ የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው የሚባል ወሬ ቢነፍስም በመጀመሪያ የተቆናጠጡት በኒያው ሊቀመንበር መስተንግዶ ኮሚቴ ኃላፊነት ሹመት አልነበረም? እንግዲህ የተቀሩት ሰብጠርጠር ተደርገው የተሰገሰጉት የአመራር አባላት ደግሞ ተወርዋሪው የፈጥኖ ደራሽ ጦር ዘረኛም፣ ፖለቲከኛም፣ የጥቅም ተካፋይም አይደለንም ለማለት በተኩላ ሰውነታቸው ላይ ለማወናበጃ ጣል ያደረጉት የበግ ለምድ መሆኑ ነው፡፡
መቼም ደብረሃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤውም ሆነ አመኔታው ጉባኤው ቅንጣት ያህል የከርስትና እምነት የሌላቸው አትራፊ ነጋዲዎች፣ በህልም የሚጓዙ ሀምበርገር ስንቁ ከአሜሪካ ሁነው ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት የተነሱ ፖለቲክኞችና ቀንደኛ የጎጠኞች ጥርቅም ነው፡፡ የምሁር መሃይማኑንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ መቼም አሁን እንደማየው ከዘመኑ ዶክትሬትና ማስትሬት ዲግሪ አለን ባዮች፣ በተፈጥሮ ልቦናውና የኑሮ ልምድ ባዳበረው እውቀቱ ተራው የሀገሬ ገበሬ ምንኛ ሊቅ ኖሯል በሉ?
ወራጁ ሊቀመንበር ለዚህ አይቀሬ ቀን ዝግጅት የጀመሩት ከረዥም ዓመታት በፊት እንደነበር አሁን ቤተክርስቲያኑ ከደረሰበት ውጥንቅጥ ውስጥ ሁነን ወደኋላ ለማየት ችለናል፡፡ እዩት እስቲ፤ ካለፈው ቦርድ ውስጥ በትክክል እኩሌታው ዘረኝነት አንገሽግሿቸው ቤቱን ጥለው ሲሄዱ ትክክለኛ እርምጃ የሚሆውነ አዲስ ምርጫ ማካሄድ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ውክልና የሰጠው ለሁሉም አባላት እንጂ ለቀሩት ብቻ አልነበረም፡፡ እሳቸው ግን በሄዱት ቦታ አምስት ሰዎች መርጠው በቦታቸው ሞሉበት፡፡ አምስት ታዛዥ ጎሮዶማኖች ማለት ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ እንግዲህ በጀመሪያ ከጊዜያዊ ኮሚቴነት ያለምንም ምርጫ በዚያው ቋሚ ኮሚቴ ይሁኑልን በሚል የጎሮዶማኖች ሆሆታ ሥልጣኑን መሶባቸው እንዳደረጉት ሲቀጥሉ ለሁለተኛ ግዜ ደግሞ እንደገና በጎሮዶማኖቻቸው ቀስቃሽነት አዛውንት የፋርጣ ተወላጆች፣ በቅነሱ አነጋገር “አባቶች”፣ የቤተክርስቲያኑ ዕዳ ተከፍሎ እስኪያልቅ ይቀጥሉልን በሚል ማወናበድ አናፍተው ለዘለቄታው በዙፋናቸው ላይ ላማጽናት ታገሉ፡፡ አሁን ላይ ደርሰን ዐይናቸንን ከከፈትን በኋላ መውረዳቸው እርግጥ ሲሆን ሁለተኛ ፕላናቸውን ተረተሩት፡፡ የፋርጣ ማፊያ ቡድን እንደገና ለሥልጣን ጦርነት ትግል ክተት ሠራዊት ብሎ ተነሳ፡፡
ያሁኑ የፍጻሜው ጦርነት ነው ብለው ላሰቡት ግብግብ ከፍተኛ ዥግጅት ተደረገ፡፡ መቼም ለነሱ ቤተከርስቲያን ምን ግዜም ቢሆን የጥቅምና የጎጥ ቦታ ነው፡፡ ከአሥር አመታት በፊት ከኢየሩሳሌም ቀጥረው ያመጧቸው የአጎታቸው ልጅ የሆኑት መሪጌታ የተገዙበትን ዋናውን የተንኮል ሥራችውን በደህና ግዜ ካደራጁት የፋርጣ ጦር መሪ ጋር በመሆን አገሩን ያተራምሱት ገቡ፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ አፋቸው በገንዘብ ከተሸበበ መዘምራን፣ ካንዳንድ ረብሻን ሲያልሙ አድርው ከሚውሉ ታክሲ ማህበራትን በክስ ከሚያምሱ ግለሰቦች፣ ከማርያም ቤተክርስቲያን ፈርጥጦ በመጣ የማይጸዳው አለቅላቂ የዘልዐለም ፖለቲከኛ አስመራጭ ኮሚቴ ሊቀመንበርነትና ከለንደን በተገዙ ሊቀጳጳስ በተጠናከረ አዲስ ምልምል የሚሊሺያ ጦር ጥቃት ተከፈተ፡፡ አሁን ትልቅ የሥልጣን ድርሻን የተጎናፃፈው የአርበኞች ግንባር የሕልም ጦር አዛዥም ቢሆኑ ባስመራጭ ኮሚቴነት ተሰልፈው ስለነበር በለስ ቀንቷቸው የራሳቸውን ተከታዮች በቦርድ አባልነት አስሾልከው ለማስገባትም ቀንቷቸው ነበር፡፡
እኒሁ ጉደኛ ሊቀመንበር ቢተክርስቲያኑ ያለሕግ መኖርም መተዳደርም ስለማይችል ከተጠየቀው ምርጫ በፊት መተዳደሪያ ደንብ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ እሱንም እኔ አውጥቼ አመጣላችኋለሁ አሉና የሆነ ነገር ይዘው መጡ፡፡ ከአፋቸው ባይወጣም፣ አሥራ አምስት አመት ሙሉ የመሩን በዘፈቀደ ያለምንም ሕግ እንዳሻቸው ሲሻቸው ከፍለው ሲሳቸው ነስተው፣ በሕዝብ ገንዘብ የዘማሪያንን፣ የጎሮዶማኖቻቸውና የአንዳንድ ጳጳሳትን ታማኝነት ገዝተው እንደሆነ ነገሩን፡፡ ትናንት የቤታቸውን ሞርጌጅ መክፈል ያቃታቸ ጎሮዶማኖች ዛሬ ጫን ያለ ቅድሚያ ክፍያ አድርገው ጫን ያለ ዋጋ የሚያወጡ መኪኖች ባለቤት የሆኑም አሉ፡፡ ማንም ሰው የማያውቀው ግን እሳቸው እራሳቸው ምን ሠርተው እንደሚኖሩ ዋና የገቢ ምንጫቸው ምን እንደሆነ ነው፡፡
አዲስ አወጣሁ ያሉትንም መተዳደሪያ ደንብም ከየትኛውም ሕግ ሆነ ከየትኛውም ልምድ ውጭ ሕዝቡ ለአንዲት ለሊት እንኳን እንዲያነበው ረቂቁ ሳይሰጠው በራሳቸው ሰብሳቢነት በራሳቸው አንባቢነት ሕዝቡ የሚያነቡትን አንቀፅ ለማብላላትም ሆነ እርስ በርሱ ለመወያየት ዕድል ሳይሰጠው አለፈ አለፈ ተብሎ በጎሮዶማኖቻቸው እየተፏጨ አፀደቁት፡፡ ይህን ሕግ ተብዬውን ለማስፀደቅ ፋርጤዎቹ ጎሮዶማኖቻቸውና የጎሮዶማኖቻቸው ጎሮዶማኖች ለመጮህም ሆን አንድን አንቀፅ ተቃውሞ የሚናገረውን አባል ለማንጓጠጥ አንድ ጥግ ነበር የተከማቹት፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የማፊያ ሥራ የሚጠበቀው ከእንደነሱ ዓይነት የእግዚአብሔርን ቤት ከሚዳፈሩ መናፍቃን ብቻ ነው ብል በፍጹም የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ምን ያድርጉ በአሁኑ ግዜ ሲኖዶሱን ካፈረሱት የነፍስ አባታቸው ከመልከፄዴቅ ዘፋርጣ ከዚህ ሌላ ምን ሊማሩ ኖሯል፡፡ ክፉ ለመዶለት፣ የተሠራን ለማፍረስ፣ የተሰበሰበን ለመበተን፣ ያማረን ለማበላሸት የተባ ምላስ የተሳለ ቁርጠኝነት ያላቸው መሆናቸውን በቤተክህነት ውስጥ ያለፈ በሙሉ ቢያውቀውም ከዚህ የጥፋት መልዕክተኝነታቸው ምን እንደሚያገኙበት የሚያውቁት ግን እራሳቸው ብቻ ናቸው፡፡ ታዲያ ዘመዶቻቸው ለምን የተለዩ ይሆናሉ ብለን አሰብን?
በዚህም የጥፋት መልዕክተኝነታቸው ነው ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ያለውን የግሌ የሚሉትን ቤተከርስቲያን የበተኑት፡፡ እጅግ በጣም የሚበዛው ምዕመን ጤንኛውን መምህር ተክትሎ ጤነኛ የወንጌልን ትምህርት ለመማር የሄደው ጥንቱኑ ያልነበራቸው ጤንነት በስተርጅና ከወዴት ያመጡታል በማለት ነው፡፡ ሲያትል ዋሽንግተን ታዋቂ የወንጌል መምህር የነበሩትን ትልቁን መነኩሴ አባ ገብረሥላሴ ጥበቡን ክመምህርነት ሥራቸው ያባረሩት ለምን እንደሆን አባራሪው እራሳቸው በውል የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ እብሪት ምን እውቀት ያሻዋል?
ወደ ዋናው ነጥቤ ልመልሳችሁና መተዳደሪያ ደንቡ እንደሆነ ሆኖ ከፀደቀ በኋላ አስመራጭ ኮሚቴውን ከጀርባ ባስቀመጧቸው ጀሌዎቻቸው አንድ በአንድ አስመረጡ፡፡ አንዱን አባል በተለይ እራሴ በሥልጣኔ ሰይሜዋለሁ ብለው አስገቡት፡፡ ከሳቸው ቃል ዊልፊጥ ለማለት የሚችል አልነበም፡፡ ወይ የሰው ባለዕዳ መሆን! ያለሳቸው ፍቃድ ፉስም ግስም የለም! አንደኛው ደግሞ የፓርቲያቸውን አባላት ለቦርድ አባልነት ያበቁ በሜዳ ላይ የሞት ሽረት ትግል ላይ የተሰለፈ ጦር አዛዥ ናቸው፡፡ ከጦራቸው ተልይተው ከተማ መሀል ምን እንደሚሠሩ ግን አትጠይቁኝ፡፡ ምናልባት ዘመናዊ ጦር የሚመራው ከኋላ ይሆን? ከማርያም ቤተከርስቲያን ስለተሰደዱት ያስመራጭ ኮሚቴ ሊቀመንበር ብዙ መነጋገር እንኳን አያስፈልግም፡፡ በደርግ ግዜ ከኢሓፓ ጀምሮ እስክ አብዪታዊ ሰደድ አምስቱም ፓርቲውች ውስጥ በአባልነት የተሳተፉ፣ በውያኔ መማክርት ሸንጎ ውስጥ አባልነት ያገለገሉ ቋሚ እምንት የሌላቸው የእርጎ ዝንብ ናቸው፡፡ አስመራጮቹን በተመለክተ ስለ አንዱ ነግሬያችሁ የነሱን ጉዳይ ላጠቃልላችሁ፡፡ ማንም መራጭ ስለማንኛውም ተመራጭ ተቃውሞ ማንሳት፣ መነጋገር፣ ጉድ ማውጣት በፍጹም እንደማይፈቀድ አስጠነቀቁን፡፡ ዋ! በሕግ እንጠይቃችኋለን አሉን፡፡ እህስ ስንል መብታችሁ መምረጥ ብቻ እንጂ መቃወምን አያካትትም ብለው የአሜሪካ ሕገመንግስት የሰጠንን የመናገርና የመቃወም መብታችንን በአንድ ደቂቃ ገፈውን አረፉት፡፡ እሳቸውም ሕዝብን አዋየሁ አላዋየሁ፣ ደሳለኝ ከፋኝ፣ ግራ ቀኝ ሳይሉ አንድ ወዳጃቸውን ለድጋሚ የቦርድ አባልነት አበቁ፡፡ እሰየው! ታዲያ ወዳጅ ለመቼ ነው?
እንግዲህ ሁሉም ተጠናቀቀና ቦርድና ሱፐር ቦርድ ሥራ ለመጀመር በቁ ማለት ነው፡፡ አዲሶቹ ባለሥልጣኖች ከተመረጡ ሶስት ወር ሊሆናቸው ምንም አልቀራቸውም፡፡ የድሮው ቦርድ ሲወርድ አዲስ ሲተካ አሥራ አምስት የተዳእፈነው ሂሳባችን ይመረመራል፣ ከሲዲ ሽያጭ፣ ለጣሪያ ማሠሪያ፣ ለከፉ ቀንም ተብሎ የተቀመጠው የድሮዎቹ የቦርድ አባላት የሚመሰክሩላቸው አካውንቶች ምን እንደዋጣቸው ሊታወቅ ነው ብለን ተስፋ አደረግን፡፡ የምናውቀውን እናሳውቃችኋለን ያሉን አፈጮማ ሊቀመንበር የሚያውቁትንና የማያውቁትን ለይተን ማወቅ አልተቻለንም፡፡ በዚህን ያህል ግዜ ውስጥ ሂሳቡን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የማወቂያ በቂ ግዜ አግኝተዋል ባይ ነኝ፡፡ ሥራው ሮኬት ሳይንስ አይደለም እኮ!! የድሮውም አዲሱም ቦርዶች የአንድ ሳንቲም አንድ ገጽታ ናቸው የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ ምነው አይሆኑ? ማዕከሉ እኮ ያው ፋርጣ መሆኑ አይደል? ሁሉም እኮ ከመልክፄዴቅ ዘፋርጣ ጋር አንድም በጥቅም አንድም በጋብቻ አንዱም በሥጋ ዝምድና የተገናኙ አይድሉ? ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ!!! ከነሱ ፍትሕን በከንቱ ጠበቅን፡፡
ገንዘብ፣ ገንዘብ አሉን፣ ስጡ፣ ስጡ አሉን፤ ከመነሻው ምዕምን እጁን የሰበሰበው እኮ ያለፈው የት እንደደረስ ሳናውቅ ተጨማሪ አንሰጥም ብሎ ነው፡፡ ታዲያ ምነው ስለዛ ፍንጭ ጠፋ? ብዙዎቻችን ከቤርሙዳ ትሪያን ግል ወጣን የሚል ተስፋችን ከንቱ ሊሆን የተቃረበ መሰለን፡፡ ጥረት አድርገው ካልተሳካላቸው ግልጽ አድርገው ለሕዝብ ማቅረብና የሕዝብን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕዝብ የመረጣቸው ለአገልግሎት መሆኑን ሳየዘነጉ አገልግሎታቸውን ቁልጭ ብሎ በሚታይ ግልጽነት ሊያከናውኑ ይገባል፡፡ ድብብቆሽ ድሮም አልረባ አሁንም አያዋጣም፡፡ አገሪቱ ውስጥ ሕግ መኖሩን መዘንጋትም ደግ አይደለም፡፡
ገንዘብ መውጪያዋም መግቢያዋም ብዙ ነው፡፡ በተቻለ መጠን መውጪያዋን ማጥበብ መግቢያዋን ደግሞ ማስፋት ብልህነት ነው፡፡ ከዚህም አንዱ መንገድ በተለያየ ምክንያት አላግባብ ተበትነው የቀሩ ገንዘቦቸን ሲቻል በውዴታ ሳይቻል በሕግ አስገዳጀነት መሰብሰብ አያስነውርም፡፡ ነውሩ የሌላን መቀማት የራስ ያልሆነውን አዘናግቶ ማስቀረት ነው፡፡ ባለፈው ጽሁፌ ልገልጽላችሁ እንደሞከርኩት በመዘምራን አካባቢ ብዙ ብር ይንከባለላል፡፡ አንድ ተረት ትዝ አለኝ፤ አባቱ ይሁን እናቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ የሚለው ብሂል እውነት ካልሆነ በስተቀር ሞቅ ያለ የሲዲ ሽያጭ ገቢ ካለበት ዘማሪ እጅ ገንዘቡን አምጣ ማለት ለምን ተፈራ? ወይስ ተደምረው ለሚያደርጉት የስም ማጥፋትና በዚህም በዚያም ዘማሪያንን ዝም ለማሰኘት የተከፈላቸው የአገልግሎት ዋጋ መሆኑ ነው? ለሎቹ በጥሬ ገንዘብ ወስደው ያቀዘቀዙትስ ቢሆኑ ለምን ዝም ተባሉ፡፡ ሱቁም እኮ ቢሆን እጅግ ብዙ ገንዘብ ይገላበጥበታል፡፡ ለምን ቀዳዳ መድፈኛ ሥርዐት አይወጣለትም፡፡ እሱም ጎጆ መውጪያነት ካልተቸረ በስተቀር?
ይቅርታ አድርጉልኝና፣ አመኔታ ኮሚቴ ማለት ምንድነው? የሚታመን ኮሚቴ ማለት ነው? በምን፣ ለምን ስለሚታመን? በቦርድና በሕዝብ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር የሚያስታርቅ ችግሩን የሚፈታ አካል ነው ነበር ነው የተባልነው፡፡ አሁን ግን እንኳን ችግር ሊፈታ እራሱ ችግር፣ ተዝቆ የማያልቅ የችግር መንስኤ ሆነ፡፡
የአመኔታው ኮሚቴ ትርምስ መፍጠር፣ የቦርዱ ከሃይማኖት ርቆ ፖለቲካ ውስጥ መዘፈቅ፣ ከአሥር ዓመታት በላይ ደከምን ታክትን ሳይሉ ያገለገሉ እውቅ ዲያቆናትና ንጹህ መነኩሴ አባት በይሁዳዊ እጅ መከራ ሲቀበሉ፣ ዐርብና ቅዳሜን ዲሲ ዳንስ ቤት አድረው ከነ ሃንግኦቨራቸው አውድምሕረት ላይ ከበሮ መታን ብለው ሲውተረተሩ፣ መቅደስ ውስጥ እዩኝ እዩኝ በማለት እንደጎረምሳ የሚያገላምጣቸው አዛውንት ካህናት ሲደማመሩ እውን እርግማን የለብንም ትላላችሁ? እግዚአብሔር እንደተወን ግን እርግጠኛ ሁኑ!!! እግዚአብሔር ቸር ነውና ፊቱን ይመልስልን ይሆናል፣ በመጀመሪያ ግን ከኛ ብዙ ይጠበቃል፡፡
ወንድማችሁ ኃይለገብርኤል ታደገ
መረጃዉ በጣም ጠቃሚ፣ ለህዝበክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን ለአገር፣ ለህዝብ ሥ እና ለወደፊቱም የአያንዳንዳቺን አቅጣትትጫ መሰረት የሚሆን ነዉና ፤ አቅራቢዉን አመሰአግናለሁ። እናንተም ደግሞ ዌብ ሳይታችሁ ላይ የሚላክላችሁን ጽሁፍ ለኣንባቢያን ብታቀርቡት መልካም ነዉ፤ካለዚያ አናንተም ከአነሱ አትሻሉም። ኣመሰግናለሁ። ዳንኤል ነኝ።
Greeting to my dear brother hailegebreal, I don’t have enough words to express my gratitude. Thank you for educating me, you are a brilliant scholar. You are a treasure keep up the magnificent work. Can you put it on you tube for more exposure? I Love You!