እግዚዮ በሉ

ይኑር ሰው ከዋሽንግተን ዲሲ

በዚያን ሰሞን በተከታታይ ሳምንት በአንዲት ትንሽ ”ቅድስት አገር” በተሰኘች ድረ ገፅ ላይ ስለ በሰሜን

ምስራቅ ዋሽንግተን ዲሲ ስለሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የሚያወሱ ፅሑፎችን አንብቤ ነበር።

ፅሑፎቹ የሚደንቁ ናቸው። ለረጅም ግዜ ከሕዝብ ተደብቀው የኖሩ እውነታዎችን ገሀድ አውጥተዋል።

የሚገርመው ለብዙዎቻችሁ አዲስ ቢሆኑም ለኔ ግን አዲስ አልነበሩም። የሆነ ሆኖ ይህንን ጉድ ሁሉ

ለብቻዬ መሸከሜ እጅግ በጣም ከብዶኝ በዝምታ በመተባበሬ ህሊናዬን እረፍት ነስቶኝ ነበር። ለፀሐፊው

ኃይለ ገብርኤል ታደገ ምስጋናዬ ይድረሰውና የሱን ምሳሌ በመከተል ይህችን አነስተኛ ፅሑፍ በማቅረብ

ከጭንቀቴ ተገላግያለሁ። ቃላትን ማቀናጀቱ ባይሆንልኝም ምንም ሳልጨምርና ሳልቀንስ ከእውነተኛ ስሜቴን

እንደወረደ አቅርቤላችኋለሁ። የተወላገደውን አቅንታችሁ፤ የከረረውን አላልታችሁ፤ የመረረውን

አጣፍጣችሁ ትረዱልኝ ዘንድ እማጸናችኋለሁ።

በመፅሐፈ ፋርጤማ ከምዕራፍ 1 ቁ 1 እስከ 13 ያለውን በመጥቀስ ልጀምርላችሁ፤

“ በቀድሞው የገብርኤል ሊቀ መንበር ላይ የወያኔ የጥፋት መንፈስ በላዩ ላይ አደረ። ይህ የጥፋት

መንፈስም እንዲህ አለው፦ መቋሚያህን አንሳ፤ ጎረደማዎችህንም ይዘህ አምባ ወደሚባል የቅዠት ተራራ

ውጣ። አዲሱንም ባይህ ሊቀ መንበርም ከአሽከሮቹ ጋር ሆነው ይከተሉህ። እሱ ፈጣንና ቀልጣፋ አጥፊ፤

ታዛዥ እንዲሁም ቀልማዳ ባሪያዬ ሆኖ አግኝቸዋለሁና። ሕዝብም በደጀ ሰላም እንዲሰበሰብ ጥሪ

ያስተላልፍ፤ እንዲህም ብሎ ይንገራቸው፤ የጥፋት መንፈስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብታለችና ይህን

ስትፈፅሙ ግን ሌብነትን፤ ውሸትን፤ መቀላመድን፤ ገንዘባችሁ አድርጉ። ነገር ግን ተጠንቀቁ! በሚሊዮን

የሚቆጠር የወያኔ ገንዘብ በዲሲ ተረጭቷል ብላችሁ አትስበኩ። ሕዝቡም አንድም ዲናር ከኔ

እንደማይወጣ ያውቃልና። ከሁሉም በላይ ግን ስብከተ ወንጌል ከምድር ገፅ ይጥፋ! ይህ ከሁሉም በላይ

የከበረ ታዕዛዜ ነው። አባቶችን አዋርዱ ጦራቸው ቀጤማ እስኪሆን ድረስ። አፋቸውንም ለጉሙ፤ ስርዐተ

ቤተ ክርስቲያን እያሉ እንዳያሳስቱ። እግራቸውንም ኮድኩዱ፤ እንዳይወጡ፤ በአካባቢያቸው ሰውም

እንዳይገባ እንዳይወጣም። የእይታ ጨረርም ላኩባቸው፤ካሜራም ይሉታል”።

ሕዝቡም ይህን በሰማ ግዜ አጉረመረመ። “እነዚህ የምናውቃቸው የሀገር ነቀዞች የቤተ ክርስቲያን

ቅንቅኖች አይደለምን? አለ።” መለየትንም ወደደ፤ እንባውንም አፈሰሰ፤ ልቡም በሀዘን ተነካ። ቤቱም

በሀዘንና በትካዜ ተዋጠ። ከሕዝቡም መካከከል እውነቱን የተናገሩ ነበሩ። ነገር ግን በአጭበርባሪዎችና

በወሮበሎች ድምፅ ተዋጡ። ሕዝቡ ግን መልሶ ወያኔ መንፈስ ነውን? ብሎ ተዛበተ።

በሀገራችን አንድ አባባል አለ። ትንሽ ሰው ትንሽ ነው፤ አንሶ ያሳንሳል ይባላል። በዚህ ቤተክርስቲያን ባለጌ

ገነነ። ትህትናን የተላበሰ በጎ ስራና ጥሩ ስነ ምግባር አይቶ ብዕሩን ሲያነሳ ብርሃን ይታየዋል መልካም

መልካሙን ያስባል፤ያሰፍራል። ነገር ግን ክፉንና ጸያፍ ስራን ሲያስተውልና ሲመለከት ደግሞ እንደዚያው

ብዕሩን አሹሎ ይህን ክፉ ስራ ይመዘግባል። አሁን እኮ የማያቸው የተረገሙ የአንድ ወንዝ ጉዶች፤ ወገንና

ዘመድን የሚያለያዩ፤ ከተሰደዱበት ሀገር እንኳን ልምድ በመውሰድ መማር ባለመቻላቸው ያበሳጨኛል።

አለመታደል ነው፤ የሀገሬ ባላገር ሲተርት “አህያ ውርንጭላ በትንሽነቱ ይዘላል ይሮጣል ይቧርቃል ከኔ

በላይ ማን አለ ይላል። መጫን ሲጀምር ግን አህያነቱን ማረጋገጥ ይጀምራል” ይላሉ። ታዲያ እነህኝን

አጥብቃችሁ ብትጭኑልኝ ማንነታቸውን ያውቁ ነበር።

ምን ያደርጋል የወያኔ ቡችላ መሆን በኬንያ ዞሮ ኢትዮጵያ እየተገባ ቤት የሚሰራው፤ ሌንቦውን ዘልጦ

ከቅድስት እስከ መቅደስ የሚያዘጠዝጠውን፤ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ ብሎ የሚያናፋውን ማየትና ወያኔ

የሰጠውን የማፍረስ አደራ ለመወጣት ሌት ተቀን ያለ እረፍት ነጋ ጠባ ሳይሉ፤ በአርዕዮስ ተክሌ እየማሉ

ቤሳቢስቲን ሳያወጡ ሙሉ ጌታ ነኝ ብሎ እየተንጎራደዱ ፤ ሕዝብ ቆሞ የሰራውን ቁጭ ብለው ሲያፈርሱ

ማን አዋየ ማን መከተ? ቂሉ ወይስ ጉዱ ካሳ? ተዉኝ ጉድ እስከ ወዲያኛው ይሉ የለ! እስቲ ፍረዱኝ፤

የሕዝብን አንድነት እንደ ቅንቅን የሚበሉ ነቀርሳዎች፤ የቤተክርስቲያን ሰላምና ፍቅርን የሚነሱ፤

አዕምሯቸው የሰባ፤ የፖለቲካ አመለካከት ብቻ ይዘው እንደ ደርግና ወያኔ እኛ ብቻ እናውቅልሃለን

የሚሉ፤ ተምረው እንዳልተማሩ እያዩ የማያስተውሉ፤ እየሰሙ የደነቆሩ፤ የደነዘዙ ግኡዝ ፍጥረቶች፤

ሰውነታቸው ብቻ አሜሪካ የገባ፤ አስተሳሰባቸው ጨቅላ የሆኑ ፋራዎች ናቸው።

እስቲ ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ስትገቡ በጌትነት ሲቅበዘበዙ ስታዩ፤ የቀበሌ ወይም የደርግ ጽህፈት

ቤት የተቃረባችሁ አይመስላችሁም? ወይንስ የአራዳ ዘበኞች ቁርስ ፍለጋ የሞቀ ሻይ ለመጠጣት ተራ

የሚጠብቁትን? እኔ እንጃ! አንድ ነገር ግን በቁጥር 1 ቦርድ ጽ/ቤት ሳልፍ አዲስ አበባ ድሮ በደርግ፤ ዛሬ

ደግሞበወያኔ ግዜ ያለሁ ይመስለኛል። የሰዎች ጠረን ተቀይሮ፤ አፋቸው ኩበት መስሎ የመንገድ ላይ

ተዳዳሪንም በመምሰል ያሳስታሉ። ወይንስ ለጽድቅ ሲጸልዩ አድረው ይሆን? ተምታታብኝ፤ የት እንዳለሁም

ግራ ይገባኛል። ድንገት ግን በጆሮዬ ሰይጣን ሹክ አለኝ። ”አልሰማህም? በዚህ የመሸገው የአፍ ነበልባል

ጦር አዲስ አበባ ያለውን የወያኔ የእናት ጦር እያርበደበደ ይገኛል። በማንኛውም ሰዓት ተወርውሮ

ሊመታውና ሊቀላቅለው ያስባል” ብሎ ደስ አሰኘኝ።

ለዚህ ሁሉ ብጥብጥና የቤተክርስቲያን መናጋት ዋና ምክንያት የሆነው የድሮ ሊቀ መንበር የቀበራቸው

የሰው ፈንጂዎች ናቸው። ከቦርድ አመራረጥ ጀምሮ አሁንም አሽከር የሆኑት ደብተራ ከለንደን ስራዬ ብሎ

በሚስጥር ያስመጣቸው ሊቀ ጳጳስ ናቸው። ይህ ሰው የሚታወቅበት ዋንኛ ባህሪው ቅጥፈት ነው። ጥዋት

የተናገረውን ማታ የሚክድ፤ ማታ የሰራውን ሲነጋ እኔ አይደለሁም የሚል፤ ተማርኩ ብሎ የሚኮፈስ፤ ነገር

ግን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይዞ ማስተዳደር ያልቻለ ግብዝ ሰው ነው። ከሁሉ በላይ ግን ሁሉን ያሳዘነና

ልብ የሰበረው ካህናትን ከመቅደስ ውስጥ በፖሊስ ያባረረ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና ሃይማኖት የሌለው

አረመኔ ሰው መሆኑ ነው። ስለዚህ ሰው ገና ያልተነገረ ብዙ ጉድ አለ። እሱን ልተውና ስለ ለንደኑ ሊቀ ጳጳስ

ላውራ። ያልታወቀባቸው የተንኮል መሀለቅ ይሏቸዋል። እንዲያውም ኩርፋፍያ የቆላ እባብ መርዙ

የማይድን ብለው ያወድሷቸዋል። እስቲ ተመልከቷቸው፤ የካህናቱን የጸሎት ልብስ እንደ ድብዳብ

በላያቸው ላይ ጭነው እንደጉርና ይገፋሉ። ስለ ክርስቶስ መምጣት ገና በተስፋ የሚጠባበቁ፤ በእድሜ

የበሰሉ፤ ስለ አዲስ ኪዳን ግን በምንም አይነት የማይታሙ፤ ወንጌል ሲነገር፤ ስለ ክርስቶስ ማዳን ሲሰበክ

የሚተናነቃቸው ናቸው። አለማወቅ ኃጢአት አይደለም። የሚያሳዝነው ግን በለንደን ተሰደው ሲኖሩ

ከአንድ ዲያቆንና ቁጥር ከማይገቡ ሰዎች ተስማምተው መኖርና መፀለይ አቅቷቸው ቤተ ክርስቲያን ተዘጋ።

አሁን በማያውቁትና ባልሰሩት ቤተ ክርስቲያን ተወዝፈው አበል እየተከፈላቸው መኖር አቅቷቸው

መበጥበጥን መረጡ። ፍትሐ ነገስት እኮ የሚለው አንድ ሊቀ ጳጳስ በሌላ ሀገረ ስብከት ሲሄድ ከሰባት ቀን

በላይ በእንግድነት መኖር አይገባውም። እኚህ አባት ( ልበላቸው ) ግን ክፍላቸው መላወሻና መተንፈሻ

እስኪያጣ ድረስ በቁሳቁስ ተሞልቶ የንግድ መደብር ይመስላል። በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ካሜራ ገባ

ብሎ ቀጣፊው ሊቀመንበር ሲደሰኩር ጉድ ፈላ አልኩኝ። ሌባና ቀማኛ ያስቀራል ብዬ ደስ ብሎኝ

አይምሰላችሁ። አንድ የማውቀው ነገር ስላለ ነው። እኒህ በኢየሩሳሌም ሳሉ ሴት መነኮሳትን አጠምቃለሁ

እያሉ የተባበሩ አሁንም በዚህ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሴቶችን እርቃነ ስጋቸውን እያሳዩዋቸው

መጠመቅ ጀምረዋል ስላሉኝ ነው። የውስጥ አዋቂዎች እንዲህ ያለ ነገር ካሜራው እንዳያነሳ ግዝት ነው

ይሉኛል። እኔ ይህንን አላውቅም ውርድ ከራሳቸው።

 

አሁን ስሰማ ደግሞ የጥንቱን የጠዋቱን የቆሎ ተማሪ ስርዐት ያልረሱ ወደ ለንደን አኮፋዳቸውን ይዘው

የእንግሊዝን መንግስት በእንተ እግዝትነ ማሪያም መኖዬ ይሰፈርልኝ ይላሉ አሉ። እንዲህ ነው

ለእግዚአብሄር መንግስት ማደር። የኩሺናው ዶክተር የሲኖዶሱ ጽ/ቤት ልዩ ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል ብሎ

ነበር። ስራ አይተጓጎልባቸውም። ዘባረቅሁ ወይስ ተማቶብኝ ነው። ቂሉ ካሳ ሆንኩ መሰለኝ።

በስደት ያለው ሲኖዶስ ፀሐፊ የሆኑት አባት ስርዐት ፈረሰ፤ ተበላሸ ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ

አይሾምም ብለው ተሰደው ራሳቸው ስርዓት አፍራሽ ሆነው ያተራምሱታል። ካልተበጠበጠ አይጠራም

የሚልም ዘይቤ አላቸው። ለምሳሌ የሲኖዶስ ድጋፍ ሰጪ ( የፖለቲካ ፓርቲ ) የአመኔታ ጉባኤ የጳጳሳትን

ስልጣን የነጠቀ ስርአተ ቤተክርስቲያንን የሚያሽመደምድ ነው። ካረጁ አይበጁ ወይስ እድሜ ዘልዛላው?

እኔ አላውቅም። ለመሆኑ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የወንጌል ገበሬዎች የት ሄዱና ነው?

በቤተክርስቲያን ውስጥ በክፋት የቆመ ቢኖር ይወገድ እያለ ገብረ ሰናየው ወይም ዋናው ቀዳሽ ካህን ቅዳሴ

ከተጀመረበት ዘመን ጀምሮ ይፀልያል። ታዲያ ምነው እየበዙ ሄዱ። ፀሎቱና ፀበሉ አልይዝ አልሰምር አለ

እንዴ? እያልኩ ጨንቆኝ የንስሃ አባቴን ጠየኳቸው። አዬ ልጄ አሉና ተገርመው፤ መጀመሪያ የሰይጣን ቤት

የት ሆኖ፤ መቅደስ እኮ ነው አሉኝ። እረፉት እንግዲህ! አንድ ነገር ግን ትዝ አለኝ። በቅዳሴ መሃል

አቋርጦ፤ ልብሰ ተክህኖውንም ወርውሮ የሄደው፤ በድፍረት ያለፍርሃት ከዲያቆን መነኩሴ እስከ ሊቃ ጳጳስ

ማይክሮፎን ከእጅ የሚነጥቀው፤ አባቶችንም ሕዝብንም የሚገላምጠው፤ ስጋ ወደሙ ሲፈተት

የሚክለፈለፈው፤ ለምንም ክብር የሌለው ደብተራ ለካስ ወዶ አይደለም በራሱ ላይ ሰይጣን ሰፍሮበት

ነው! እግዚኦ በሉ፤ እንዲህ ያለው ቀጣፊና ቀልማዳ የጋኔን ቤት ነገር ሰሪ ማስወጣት ነው እንጂ መዳኛም

የለው። በአውደ ምህረት በኩልም ብዙ ጉድ ታያላችሁ። ዳዊት ስለፈጣሪው እየዘለለ የክብር ልብሱን ጥሎ

ራቁቱን እስኪሆን ድረስ ዘመረ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ ይለዋል። ዛሬ ደግሞ የገብርኤል መዘምራን

ምን እንደነካቸው አላውቅም እናሸንፋለን ሆኗል። አብዮት አደባባይ ያለሁ ይመሰለኛል። አንዳንድ ግዜም

የጠራ ስድብ ናዳ ሲወርድ የመሸታም የቃልቻም ይመስላል። ግራ የሚያጋባ ሆኗል።

ከበሮ እየደለቁ እንጡርብ ቢዘሉ፤ ማሲንቆ ይዘው ቢገዘግዙ ዕዳ እንደሁ ከራስ አይወርድም። የወንጌልን

ትምህርት ንቆና አቃሎ ብሎም ረግጦ በትዕቢት እንደ ግድግዳ ቆርቆሮ መጮህ አይጠቅምም። የልጆችን

ጨዋታ ልተውና የምስራች ልበላችሁ። በናፍቆት የምንጠብቀው እናንተ በሌለ ነገር ታምናላችሁ እያሉ

የሚመጻደቁት የደርግ አቀንቃኝ የነበሩት እመቤት ንስሀ ገቡ መሰል ለእኔና ቤተሰቤ መልአኩ ገብርኤል

የሰራልኝን እኔ ነኝ የማውቀው ይሉናል።ለማያውቁሽ ታጠኚ፤ አርፈው ይቀመጡ።ይልቅስ ንስሀ ገብተው

የቀረ ዘመንዎን፤ የልጅ ልጆችዎን ለበረከት እንዲበቁ ቢቀበልዎት ይጸልዩላቸው። በየስብሰባው ላይ እኔ ነኝ

ተዘራ አይበሉ። አይቀላምዱ። የዘመድ ምክር ይስሙ።

ለሁሉም እስቲ ነገሬን ልቋጭና በገብርኤል በኩል የታዘብኩትን ላልነበራችሁ ላውጋችሁ። ጊዜውንና ሰዓቱን

ጠብቆ ተዓምሩን ሠራ ማለት ይቻላል። የብዙ ሰው ሀብትና ጉልበት ፈሶበት የተሰራው ቤt ክርስቲያን

ውስጥ ጥገኛና እንደ ውጭ ሰው የሚታይበት ሆኖ የቆየው ምዕመን ብሶቱ ፈንድቶ ብሶቱን በአውደ ምህረት

ላይ ተንስቶ አሳየ። አንዳንድ እንደ ግል ሀብት የያዙት ግለሰቦች እንደሚሉት መንበሩ ተደፈረ እውነት

ተናገሩ፤ ለምን ይህን ያህል እንዲደፈር ተነሳሳ? ጳጳሳትም ሆኑ በተለይም አቡነ መልከ ጻድቅ የቦርድ

አባላትና ደጋፊዎቻቸው መመለስ የሚገባቸው ይህንን ነው። ጥያቄ ለመመለስ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።

ስርዐተ ቤተክርስቲያን ማስከበር በሚገባቸው ሊቀ ጳጳስ በየግዜው ተጣሱ፤ ሹመት ያለአግባብ ለሌላ ሰው

ተሰጠ፤ የወንጌል አስተማሪው ተባረረ፤ 16 አመት በአቀኑትና በሰሩት ቤት ስርዓት ተጣሰ ቢሉ ተባረሩ፤

የ18 አመት የቤተ ክርስቲያን የአካውንት ሂሳብ በማያሳምን ምክንያት በሊቀመንበሩና በሂሳብ ሹሙ እጅ

ብቻ አካውንት ተከፍቶ ተቀመጠ፤ የቦርድ አባላት በአሻጥር እንደ ፖለቲካ በማጭበርበር ተመረጡ፤ የቤተ

ክርስቲያኑን ደንብ በሰዓታት አጣድፈው ብዙ ሰው በሚገባ ተረድቶት ሳይመጣ አለፈ። ይህም ህግ

የቤተክርስቲያንን ህግ ጨርሶ የተጋፋና የካህናትን ስልጣን የሚቀማ አመኔታ ጉባኤ ብለው አዲስ ህግ

ጣሉበት። በተለይም የድሮ ሊቀመንበር ከመቅደሳቸው ጳጳሳትንና መነኮሳትን በፖሊስና በደብዳቤ ከግብረ

አበሮቹ ጋር አባረሩ። አሁን ያለው የቦርድ አባላት ጨርሶ የሕዝብ አመኔታ ያጣ እንደፈለገው የንግድ

ድርጅት የሚመራ፤ከሁሉም በላይ ደግሞ አባላትን የማስጠንቀዊያ ደብዳቤ በመጻፍ እንዲሁም በቴሌፎን

ማስፈራራት ጀምሯል። ቤተክርስቲያን መግቢያ ላይም ምዕመንን የሚያስፈራሩና የሚገላምጡ

ተቆጣጣሪዎች አቁመዋል። ይህንን ሁሉ ግፍ ተሸክሞ ምዕመኑ በትዕግስት መቆየቱ ያስመሰግነዋል።

መንበሩን ተዳፈሩ ብለው የሚያስወሩትም መንበሩን እኮ የሚያዋርደውም ሆነ የሚያስከብረው ሕዝብ

 ብቻ ስለሆነ በኃላፊነት የተቀመጡትም ስነ ምግባር ነው። እንደዚህ ከቀለሉና ማን አለብኝ የሚሉ ከሆነ

የህዝብ አመጽ መቀስቀሱ አይቀሬ ነው። ምን አጠፋን ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ነው።

ወደ ሀገራችን ልመልሳችሁና አቡን (ጳጳስ ) የረገጠውን መሬት የሚስም ልቡ በትህትናና በፍቅር የተሰበረ

ነበር። የአሁኑ ሊቀ ጳጳስ ራሳቸው አጥፍተው እናንተ ይቅርታ ጠይቁ የሚሉና ከሳንዲያጎ፤ ካሊፎርኒያ

ማባረሪያና መሻሪያ ደብዳቤ የሚልኩ ናቸው። ታዲያ እንዴት ነው እኚህ ሰው የሚከበሩት?

ሌላው ነገር ደግሞ፤ ነብሰ ገዳይ የቤተ ክርስቲያን ደወል ደውሎ ምህረት የሚሰጥበት ስፍራ ነበር። አሁን

ግን ከካህን እስከ ምዕመን የሚባረርበት ሆኗል። ታዲያ መጮህ ይነስ? ለቆ መውጣት ይነስ? እስቲ

ፍረዱ!ይህ ቤተክርስቲያን የሚከተለው የጥንቱን የጠዋቱን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስርዓት ነውን? ሀሰት!

ዛሬ ማስቀል የያዙ የክርስቶስ አገልጋዮች ተቀምጠው ሳምሶናይት ይዘው በአባቶች የሚነግዱ ቦርድ

የሚባሉ የዘመኑ ፈሪሳውያን ናቸው። እግዚኦ በሉ! ቤተክርስቲያንን ከጥፋት መልሱ። ለልጅ ልጆቻችሁ

የማቆየት ኃላፊነት አለባችሁና።

Posted in Uncategorized | Leave a comment

አላቅሱን!

               መቼም የዋሽንግተን ዲሲው ደብረሃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተከርስቲያን ጉዳይ ተወርቶ የሚያልቅ አልሆነም፡፡ አንዱን ሲይዙት ሌላ ጅራት ያወጣል፡፡ ባለፈው ለንባብ ባቀረብኩላችሁ “እውነትን ሰቀሏት” በሚለው ጽሁፍ ላይ በታህሳስ ቅዱስ ገብርኤል ሥርዓተ ንግስ ላይ ታቦት ከመውጣቱ ቀደም ብሎ ምዕመናን ለዓመታት በደከሙበት፣ ጉልበታቸውንም ሆነ ግዜያቸውን  ጭምር የከሰከሱበት ቤተክርስቲያን ከክርስቲያናዊ እምነት ውጭ በአጉል መሪዎች አግድም እየተመራ በክህደት ቁልቁለት ሽምጥ እየጋለበ መሆኑን ለማሳወቅና ከተቻለም የተሻለ አቅጣጫ ለማስቀየስ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ወርቃማ ዕድል ገጥሟቸው ነበር፡፡

                 ምዕመናን በዕለቱ ተገኝተው ለነበሩት ትልቅ እንግዳችን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ፣ ደርጉ/ቦርዱ የፈጸመውን በድብቅ የሰባኬ ወንጌሉን የክህነት ሹመት መከልከልና ከሥራ መታገድ ምክንያት እንዲገለጽላቸው ተማፅነዋል፡፡ እርምጃው የቅስና ሰጪውን ሊቀጳጳስ ሥልጣንም ጭምር በእብሪት የተጋፋና የምዕመኑንም የበላይነት እንደዋዛ ያየ አምባገነንነት እየሰፈነ መሆኑንም ያስተጋባ በዕለቱ በቦታው ለነበረውም ሆነ ለሰማው ሁሉ ግልጽ ሆኖ ታየ፡፡ ዲያቆናቱም  የወንድማቸውን የሰባኬ ወንጌሉን ከሥራ መታገድ አስመልክቶ የሥርአቱ መጣስ ለውደፊቱ ሊያመጣ የሚችለው ቀውስ ከወዲሁ ስለታያቸው እጃቸውን ታጥበው ከደሙ ንጹህ ነን ብለው ዕለቱን በየቤታቸው ማሳለፉን መርጠው ነበር፡፡

           ጉዳዩን ካለፈው ጋር ላያይዝላችሁ ብዬ እንጂ ላወጋችሁ ያሰብኩት እንኳን ሌላ ነው፡፡ በተሳካ ሆኔታ የተከናወነው ተቃውሞ ከጎሮዶማኖቹ አኳያ እንዴት እንደተገመገመ ላሳያችሁ ነው የተነሳሁት፡፡ መቼም ያ ዘረኛ ቡድንና ጭራዎቹ በጣም የሚፈሩትና የሚጠሉት ጉዳይ የሥራችውን ገሃድ መውጣት እንድሆነ ለናንተ አልነግራችሁም፡፡ ሥራቸው ጨለማን ተገን አድርጎ፣ እያደባ የሚሽሎከለክ፣ ሸምቆ የሚያጠቃ፣ ተደብቆ የሚነጥቅ፣ የምዕመንን ገንዘቡንና ስሙን  እንደ ሥጋ የሚቦጭቅ በመሆኑ የዕኩይ ሥራቸው ለሕዝብ መገለጥ እስከ ገሀነም ድረስ ያስበረግጋቸውል፡፡ መቼም ትውውቅ የሚኖራቸው ያው ከገሃነም ጋር ነው ብዬ ነው፡፡ የገነት መንገድማ ጉዞውን በግልጽ፣ በብርሃን፣ በፀሐይ፣ ለሚያደርግ አማኝ ነው፡፡

           ትልቁ ጥያቄያቸው፣ ምነው ሌላ ግዜ ከቅዱስ ገብርኤል ንግስ ቀን ውጭ ቢያደርጉት? ሕዝበ ክርስቲያን ከየእስቴቱ በተሰበሰበበት፣ የአገር ሁሉ እይታ እኛ ላይ በሆነበት ዕለት እኩይ ድርጊታችንን አደባባይ አወጡብን ነው ቁጭታቸው፡፡ ምነው እርስበራሳቸን ብንነጋገርበት ሁሉ ብለዋል አሉ፡፡ እውን እነሱ ለመልካም ምግባር ሊቆሙ? በሰላም ለሰላም ሊወያዩ? ምነው ምርጫው የተካሄ ሰሞን አሸናፊ ፓርቲ ነንና ያሰኘንን እናደርጋለን፣ ፕሮግራማችንን እናስፈጽማለን ሲሉ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ስለ ሰላም አወሩ? ምዕመኑ የት ይደርሳል፣ ምን ሊያመጣ ያሉቱ ናቸው ወይስ የነሱን ተንኮል በሹልክታ የሚያራምዱላቸው በእግራቸው ሌሎችን መለመሉ? ፕሮግራማችንን እናስፈጽማለን ያሉትስ የትኛውን ፕሮግራም ነበር? ይሄን የወንጌል መምህሩንና ዲያቆናቱን ያባረሩበትን ፕሮግራም ነው ወይስ ሊቀጳጳሱን ለማባረር የሚያቅራሩበትን ነው? በምዕመኑ ላይ ጦር የሚሰብቁበትም አንዱ ፕሮግራማቸው ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ፡፡ የሚሰብቁትን ጦር ግን መቼ እንደሚወርውሩት ስለማይታወቅ ምዕመን ከወዲሁ ሊዘጋጅበት ይገባል፤ ያላወቁ አለቁ ነውና ነገሩ፡፡ ዲቁናውን፣ ቅስናውን፣ መምህርነቱንና ጵጵስናውንማ በሱዳን ሻይ ቤቶች ተሹመውት ሊሆን ስለሚችል በቤተክርስቲያኑን የመንፈሳዊ ሥራውን ማካሄድ እንኳን ብዙም አይገዳቸውም፡፡ ለካ ፈረንጅ ትንሽ እውቀት አደገኛ ነው የሚለው እውነቱን ኖሯል!

           ሁለተኛው ጥያቄያቸው የገንዘብ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ቅዱስ ገብርኤልን ብሎ ከሚመጣው አማኝ ሕዝብ ገንዘብ በገፍ በአካፋ ለማጋበስ የተዘጋጁበት ቀን ነበር፡፡ የገንዘብ ነገር መቼም ሞታቸው ነው፡፡ በሙዳየ ምጽዋት መድረቅ ጉዳይማ ሲበሳጩ፣ ሲቆናጠሩ፣ በአውደ ምህረት ላይ ሲሳደቡ፣ አንዴ ውቃቢ አለባችሁ አንዴ በጥሩ ቤት ውስጥ ኖራችሁ እያሉ ሲሳለቁብን ሰነበቱ፡፡ ገንዘባችንን ከኪሳችን የማውለቅ ያህል ወረዱብን፡፡ አስፈራሩነ! ይሄን ሲሉ ጭራሽ ዋናው ገንዘብ መሰብሰቢያው ቀን ላይ ያላሰቡት ዱብዳ ገጠማቸው፡፡ ምዕመንን ለማስፈራሪያ ያቆሙት የፖሊስ መኪናም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አልረባቸውም፤ እርግጥ የመበራቱ መብለጭለጭ ለበዓሉ ድምቀት ይሰጠዋል ብለው ካልሆነ በስተቀር፡፡ ግራ በመጋባት እራሳቸውን ሲያኩ የዋሉበት ቀን ሆነ፡፡

             በዚህ ሁሉ ላይ እንግዲህ ሰዉን ሁሉ አንድ በአንድ ሲያወግዙ ሲሳደቡ ሲተናኮሉ አንድም ግዜ እራሳቸውን  አንድ ትልቅ ጥያቄ ጠይቀው የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ እኛ የት ላይ ተሳሳትን? ምን አጠፋን? ምዕመን ለምን አንቅሮ ተፋን? የሚል ጥያቄ  በመካከላቸው አንስተው ተወያይተዋል የሚል ግምት በፍጽም የለኝም፡፡ ምን አጥፍቼ ይሆን፣ ምን በድዬ፣ የት ላይ ተሳሳቼ ይሆን የሚል እራሱ የከበደው የጨዋ፣ የትሁት፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት/ያደረባቸው ህሊና ያላቸው ሰዎች አካሄድ ነው፡፡ የለም፣ ረጋ በሉ፣ የያዝነው መንገድ የጥፋት መንገድ ነው ብሎ የሚመክር፣ የሚገስጽ አዕምሮ ያለው እመሃላቸው ባለመኖሩ ተያይዘው፣ ቤተክርስቲያኑንም አጥፍተው ሊጠፉ የጥፋት አፋፍ ላይ ቆመዋል፡፡ መንገዳችን እየቅል ስለሆነ፣ ቤተክርስቲያን የሚመጡበትን ዋናውን ምክንያት በትክክል ማስቀመጥ ተሳነን እንጂ፣ እግዚአብሔርን ለማምለክ እንዳልሆነ ግን ለረዥም ዓመታት አካሄዳቸውን የተከታተልነው ቀርቶ ሌላውም ይገነዘበዋል ባይ ነኝ፡፡ የሚያሳዝነው ሁኔታ ቦርዱም የነሱን ዓይነት ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ለነገሩ እነሱ ከፈጠሩት ቦርድስ ምን ሊጠበቅ ይችላል? አመኔታው ጉባኤስ ቢሆን በየቦታው እየዞረ የሰው ስም ከመለቅለቅና አውደምሕረት ላይ ቆሞ ምዕመንን ከመዝለፍ  ሌላ ምን ጥሩ ነገር ታየበት? ማንን አስታረቀ? ማንን አስማማ? እየዞረ የሰው ሥጋ የሚበላው ይሄው ከራሱ የተጣላ አመኔታ ጉባኤ አይደለም?

           የንግሱ ዕለት ነገሩ የተበላሸብኝ፣ ለኔ ማለቴ ነው፣ ገና ወደ ቤተክርስቲያኑ ልገባ ደረጃውን ስወጣ ነበር፡፡ ያለቦርዱ ፍቃድ ፎቶግራፍ፣ ቪዲዮ ምናምን ማንሳት ክልክል መሆኑን ያበሰረችዋ ማስታወቂያ የነበረኝን ጥሩ መንፈስ ሰረቀችብኝ፡፡ ቤተክርስቲያን የጦር ካምፕ አይደል፣ ሚስጥራዊ የምርምርና ሥርጸት ማዕከል አይደል፣ ምዕምኑ ላይ በገዛ ቤቱ የዚህ ዐይነት ማዕቀብ መጣል በነሱ ቤት እግዚአብሔር የሚወደው ደግ ሥራ መሆኑ ይሆን?  ምናልባት በሻለቃ መልከፄዴቅ የሚመራው የስም አይጠሬ ወረዳ ኮማንዶ ጦር ነጋ አልነጋ ብሎ ምድር ሰማዩ ሳይላቀቅ ቤተክርስቲያኑን ሊያጠቃ ከሚችለው ከሱዳን ጦር ለመከላከል መቅደስ ውስጥ መሽጎ ይሆን? ማን ያውቃል! የእግዚአብሔር መንገድ እስካሁን ካልገባቸው ደግሞ ካሁን በኋላስ ይዋጥላቸዋል ብላችሁ ነው? ብቻ ለማንኛውም እኔም አዲሰ ትምህርት ቀሰምኩ፤ እነሱ ከሻይ ቤቱ ውስጥ ወጡ ማለት ሻይ ቤቱ ከነሱ ውስጥ ወጣ ማለት እንዳልሆነ ዘግይቼ ተረዳሁት፡፡

           ታዲያ የዛችን አሳዛኝ ማስጠንቀቂያ ይዘት በትካዜ ሳውጠነጥን መኪና ማቆሚያው አካባቢ የነበረው ከወትሮው ሞቅ ያለ ግርግር ትኩረቴን ሳበው፡፡ ለመኪና ፓርኪንግ ዕርዳታ የተሰለፉት ሰዎች በብዛት ከዚህ በፊት አይቻቸው የማላውቅ አዳዲሶች መሆናቸውን ተመለከትኩ፡፡ በሌላው አቅጣጫ ደግሞ በአንድ ቫን ሞልተው የተቀመጡ ሰዎችን ስመለከት ከሌላው ግዜ የንግሥ በዓል የተለየ ምን ጉዳይ ተፈጥሮ ይሆን ብዬ በልቤ ሥጋት አደረብኝ፡፡ ወደ ውስጥ ስገባ ኮሪዶሩን ግራና ቀኝ የተኮለኮሉትን የወትሮዎቹን መንደር አባጮች ስመለከት ውጭ የቆመው ቡጭቅጫቂ ጦር የነሱ የይድረስ ምልምል ሚሊሽያ መሆኑን ያለምንም ጥርጥር አውቅኩት፡፡ ግን ለምን ተጨማሪ ሃይል አስፈለጋቸው? ምዕመናን እኮ ቤተክርስቲያን የሚመጡት እግዚአብሄርን ለማምለክ እንጂ እንደነሱ ለውጊያ ወይም ለዕኩይ ተግባር በፍጹም አይደለም፡፡ በሠላም እናምልክበት እንጂ ከክትፎው ከጥብሱ ከምትበሉት አካፍሉን አላሉም፡፡ እሱን ለናንተም ባረጋላችሁ፡፡

           እነዚህን የበጥባጭ ጦር አባላት ምዕመን በሙሉ ማንነታቸውን በውል አውቆታል፡፡ እውነቱን ለመናገር ባለፈው ምርጫ ካከናወኑት የሸፍጥ ሥራ በኋላ ቤቱ ውስጥ ጉዳቸውን የሚያውቅ በሙሉ ዐይኑ እያየ ጆሮው እየሰማ ወድቃችሁ ተነሱ የሚላቸው ማንም የለም፡፡ ቡድናቸው እንግዲህ በቀጥታ በቦሌ ሳይሆን ለማስመሰል በሽንጥ በጅቡቲ ወይም በናይሮቢ አዲስ አበባ ገብተው መሬት ተቀብለው በማህበር ቤት በመሥራት ላይ ያሉ፣ የዕድር ገንዘብ ወደግል ኤቲኤምነት የቀየሩ፣ የታክሲ ማህበራትን በክስ የሚያምሱ፣ ሕጋዊነት የሌለው የሲኖዶስ ድጋፍ ሰጪ ግብረሃይል አባል ነን ብለው በተላላኪነታቸ የሚኮሩ ከንቱዎች ናቸው፡፡ በቀላማጅነት ተኮንኖ ጎንደር ከተማ መሀል ጀርባውንና መቀመጫውን  እንደ ህፃን ልጅ ተገርፎ ባደባባይ ተደፍቶ ይቅርታ የጠየቀውም እንዳለበት እናውቃለን፡፡ በአዲስ አበባና በጎንደር ገስጋሽ የቀይ ሽብር ተዋናዮችንም ያቀፈ መሆኑ የሁሉም ሚስጥር ሆኗል፡፡

           ይህ ቡድን ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ ለተከታታይ ሳምንታት ከሰባ ስምንት ግዜያት በላይ በተለያዩ ቦታዎች እየተሰባሰበ፣ እወደድ ባይ አባላትን በአስመራጭ ኮሚቴ አባልነት ምርጫውን ያለ ምንም ይሉኝታ ወደ ፈለጉት አቅጣጫ እንዲመሩላቸው ሲሰይሙ፣ ተመራጮችንም እዚያው ተከታታይ ስብሰባዎቻችው ላይ ወስነው የሥራ ድርሻቸውንም አደላድለው የመጨረሳቸው ዜና ያኔውኑ ነበር የደረሰን፡፡ ይህ ድርጅታዊ አሠራር ከእንደነሱ ዓይነት ሞራለ ልል ግለሰቦች የምንጠብቀው ቢሆንም እንዲያው ምናልባት የያዘቸው አባዜ ገለል ብሎላቸው እንደሆን የሚል ትንሽ ተስፋ አለመቁረጥ በምዕመኑ ዘንድ አድሮ ነበር፡፡  የለንደኑም ጳጳስ ለተወሰኑ ግዜያት በዚሁ ባልተቀደሰ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ሆነው እንደነበርም ሰበር ዜና በግዜው ደረሰን፡፡ ታዲያ ሰባ ስምንት ግዜ መግተልተል ያሰፈለጋቸው እነዚህን ድኩማን ለመምረጥ ነበር? ሥልጣኑን የፈለጉት በደካሞች ተንተርሰው ኤኮኖሚያዊና ጎጣዊ መርሀግብራቸውን ለማስፈጸም ከሆነ ካለፈው ያፍዝ ያደንግዝ አገዛዝ ብዙ ተምረናልና ምላሹ ቀላል ይሆናል ብለው እንዳያስቡ፡፡

           ስደተኞች ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞቼ፣ እንግዲህ በዚች በአሁኗ ወቅት መንታ መንገድ ላይ ደርሰናል፡፡ መንግዶቹ  አንዱ ወደ ጥፋት ሌላው ወደ መዳን የሚወስዱ ናቸው፡፡ እኛ የስደተኛው ሲኖዶሰ ተከታይ የሆነው ሕጋዊ የሃይማኖታቸን ተወካይ መሆኑን በርግጥ ስለምናምንበት ነው፡፡ አለኝታችን ብለን የምናምንበት ስደተኛው ሲኖዶሳችን ልጅነቱን እንኳን ሳይጨርስ በዐይናችን እያየነው በህቅ እንቅ እየቃተተ ወደ ህልፈት በማዝገም ላይ ይገኛል፡፡ የግሌ ሲኖዶስ ነውና እኔ እንደፈለግኩት  በጭንቅላቱ ካላስኬድኩት አፈርሰዋለሁ አስፈርሰዋለሁ ብለው ቤቱን ሊበትኑት ቆርጠው የተነሱት የጦሩ ሰው ሻለቃ መልከፄዴቅ ናቸው፡፡ እያንዳንዱን ቤተክርስቲያን እየዞሩ ማበጡን ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ ሁሉም ቦታ ላይ ሲበጠብጡ ቦርዱን አቅፈው ሕዝቡን ገፍተው ነው፡፡

           ዴንቨርን፣ ሲያትልን፣ ሳንዲዬጎን፣ ኦክላንድን የማይጠፋ እሳት የማይበርድ ጥላቻ ለኩሰውበታል፡፡ ዋሽንግተን ዲሲን ደሞ ሕዝቡን በጎጥ ከፋፍለው፣ በክፍለሀገር ሳይሆን በመንደር፣ ለመናከስ አብቅተውታል፡፡ ምዕመን በዐይኑ ሊያየው የማይፈልገውን የድሮውን ሊቀመንበር ዘመድና ጉዳይ አስፈጻሚ መሪጌታ ከሀገረስብከቱ ኃላፊ እውቅናና ከቅዱስ ከፓትርያርኩ አዎንታ ውጭ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አድርገው ሹመዋል፡፡ ምዕራብ ባሕር ዳርቻ (ዌስት ኮስት) ካለው ሀገረ ስብከታቸው ተነስተው አያገባቸው ገብተው፣ ምሥራቅ ባሕር ዳርቻ (ኢስት ኮስት) በሌላ ሊቀጳጳስ ሀገረስብከት ውስጥ በአምባገነንነት ሹመት ሰጡ፡፡ እውን ይሄ አምባገነንነት ከእግዚአብሕር ነው ትላላችሁ? አሁንማ እሳቸውን እንደእግዚአብሔር የሚያመልክ ግልብጥ የባሃዪ እምነት ተከታይ  አማቻቸው የሊቀመንበርነቱን  ቦታ ስለያዘላቸው ሜዳውም ፈረሱም በጃቸው ገባ፡፡ ከክፉዎች መንገድ እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡ እኒህን ጎጠኛ የጥፋት መልዕክተኛ ከጥፋት መንገዳቸው ባስቸኳይ የሚመልሳቸው ካልተገኘ ባጭር ግዜ ውስጥ የሲኖዶሱ ሥርዓተ ቀብር ላይ እንደምንቆም በርግጠኝነት እነግራችኋለሁ! የፊታችን ዓርብ ደሞ ወደ አውስትራሊያ ሊያቀኑ ነው ተብሏል፡፡ መከረኛ አባ ወልደትንሳኤ አያልነህ ስንት ደክመው፣ ወጥተው ወርደው፣ የስንቱን ፊት አይተው በስንት ዓመት የሰበሰቡትን ሕዝበ ክርስቲያን ባንድ ጀምበር ሊበትኑት ሊያፈርሱባቸ ነው፡፡ ማፍረስ የለመደ እርካታውን የሚያገኘው ከማፍረስ ስለሆነ ከሳቸው ጉዞ በጎ አይጠበቅም፡፡ ቤተክርስቲያናችንን እግዚአብሔር ከአጥፊዎች ይጠብቅልን፡፡

                 ሰው ትክክለኛ ባሕሪው የሚታወቀው በፈተና ወቅት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ፈተና ታዲያ በመከራ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሃብትም ሥልጣንም ለሰው ፈተናዎች ናቸው፡፡ ምንም ከሰውየው ጋር ቅርብ ግንኙነት ባይኖረኝም፣ የሰበካ ጉባኤ ሊቀመንበራችን ምን ያህል ትህትናቸው የተደነቀላቸው የተወራላቸው እንደነበሩ ግን አውቃለሁ፡፡ ያ እውነት ከነበረም አሁን ደግሞ የሚሳዩን ግልባጩን መሆኑ ነው፡፡ እቺም ሥልጣን ሆና ከመቼው ልባቸውን እንዳሳበጠችው ሳስበው ያስደንግጣኛል፡፡ አውደምህረት ላይ ቆመው ወሬኛ ናችሁ ለማለት፣ ገደብ-የለሽ የስልክ ኮንትራታችሁን (አንሊሚትድ) ቀንሱት ሲሉን በጥፊ የመቱኝን ያህል ማመን ተሳነኝ፡፡ ክሳቸው አፍ የወጣም አልመሰለኝ፡፡ ዕብሪት ክሥልጣን ጋር ተደርቦ ይመጣል የሚሉትን ነገር እውነትነት አስመሰከሩ፡፡

                 በወሽመጥ የተተከለ የመልከፄዴቅ ሹመኛ አስተዳደሪ ተብዬ መሪጌታም ቢሆኑ በሚያሳዝን፣ እስከወዲያኛው ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ በትናንትናው ሰንበት ዕለት አውደምህረት ላይ ቆመው በቤተክርሰቲያኑ ውስጥ ቪዲዮ ካሜራ የመጠመዱን ፀረ-ክርስቲያናዊ ዜና በታላቅ ምጸት አበሰሩልን፡፡ ተጠንቀቁ፣ ልብ በሉ እንቅስቃሴያችሁን በሙሉ፣ የምታደርጉትንና የምታውሩትን ሁሉ እንቆጣጠራለን እናዳምጣለን ነበር ያሉን፡፡ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ የዘላበዱትን ሁሉ እኛም በሞባይል ስልክ አስቀርተነዋል፡፡ ለመሆኑ መቅደስ ውስጥም ቪዲዮ አስገቡ ማለት ነው? እነዚህ ሰዎች ያለንበት አገር በምስለኔ የሚተዳደር ይመስላቸው ይሆን? ያለንበት አገር እንጂ መንደር እኮ አይደለም! ሕገመንግስት እኮ አለው! የሀገሪቱን ሕግ እስካልጣሱ ድረስ ዋይት ሃውስ፣ ኮንግሬስ ውስጥ መጮህ መቃወም መቻሉን አልሰሙም ማለት ነው? ፕሬዚዳንቱን መሳደብም ጭምር እንደሚቻል አያውቁም? ኧረ ከማን ጋር ነው እየተነጋገርን ያለነው እባካችሁ? ለመሆኑ ብንነጋገር ምን ሊያደርጉን፣ ምን ሊያስደርጉን ይሆን? ኧረ በባዲራው!

           የራሳቸውን ሳይወጡ ለሌላው ካህን ለመሆን ባልተንጠራሩ! ፉከራቸውን ወደጎን አድርገው በመጀመሪያ ቤተክርስቲያን ታይተው የማያውቁ አራት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ለቤተክርስቲያን ባበቁ! ወይስ እምነታቸው የኖሩበት አገር የይሁዲ ነው? ክርስቶስ ገና ይወለዳል ብለው ይጠብቃሉ ማለት ነው፡፡ ይቅር ይበላቸው!

           እንግዲህ ወንድሞቼ፣ እህቶቼ፣ እናቶቼና አባቶቼ፣ ካካባቢው ለሥራ ጉዳይ ወጣ ስለምል ከሥራዬ በቀር ለሌላ ብዙም ግዜ አላገኝምና ለትንሽ ግዜ እለያችኋለሁ፡፡ ፋታ ካገኘሁም በተቻለኝ መጠን ጆሮዬን አስልቼ አዲስ ጉዳዮችን ለማዳመጥ እሞክራለሁ፡፡ ለክፉውም ለደጉም (ደግ ባይኖርም) እራሳችሁን ጠብቁ፡፡ በሠላም ቆዩኝ፡፡

 ወስብሃት ለእግዚአብሔር

 ወንድማችሁ ኃይለ ገብርኤል ታደገ

Posted in Uncategorized | 1 Comment

እውነትን ሰቀሏት!

             የዋሽንግተን ዲሲ  ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አመራር  አካል ከትናንት ወዲያው ትናንት፣ ከትናንቱ ዛሬ በሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት የማን አለብኝነት በደል እየዋለ እያደረ በየእለቱ እያየለ እየከፋ እየከረፋ መጣ፡፡ ከቀድሞው የቦርድ ሊቀመንበር ጋር የውረዱ አልወርድም እንካሰላንቲያ ከተጀመረ ግዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ቤተክርስቲያኗ እንደተናጠች አመት ያህል አስቆጠረች፡፡ ባለፈው ጽሑፌ እንዳመላከትኳችሁ አዲሱ ቦርድ የቀድሞው ሊቀመንበር ጥቅም አስከባሪዎችና የአዲስ ፖለቲከኞች መጢቃ ነው፡፡ የቀድሞው ሊቀመንበር ዋና ጥቅም አስከባሪ አድርገው ያሰቧችውን ደብተራ በባለግልሲኖዶሱ በሻለቃ መልከፄዴቅ የቤተክርስቲያኗ  አስተዳዳሪ አድርገው ሲያስሾሙ የተቀጣጠለው የተቃውሞ እሳት ላይ ቤንዚን እንደመቸለስ ሆነና እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ ተዛመተ፡፡

                 ከኢራቁ ሳዳም ሁሴን፣ ከሊቢያው ጋዳፊ፣ ከግብፁ ሙባረክ የታሪክ መጽሐፍ ላይ አንዱን ገጽ ገንጥለው በመውሰድ ለራሳቸውም ያልበጀውን የማንጠይቆኝ አገዛዝ ይሁነን ብለው ተያያዙት፡፡ ለጥፋት ተግተዋልና ከዚያ በኋላ የተጻፈውን የአወዳደቃቸውን  ገጽ ለማንበብ ግን ዝንባሌም ግዜም አልነበራቸውም፡፡ ባለፉት አሥራአምስት ዓመታት ውስጥ በምንም መልኩ ሃሳቡን ተጠይቆ፣ አስተያየቱን ሰጥቶ፣ ስሜቱን እንዲተነፍስ ያልተፈቀደለት ምዕመን አምላኩን ፈርቶ የተላበሰውን ዝምታ እብሪተኞች እንደፍርሃት ቆጠሩበት፡፡ መቼም ልብ ሲያብጥ ድፍረት ይሰማልና በስተመጨረሻ የወንጌል መምህሩንና ለአሥራ አራት አመታት ያለምንም ክፍያ ያገለገሉ አራት ዲያቆናትን ከመቅደስ ለማሰናበት በቁ፡፡ ቤተከርሲቲያኑ የራሱን ሕንፃ ከመግዛቱ ቀደም ብሎ፣ እነዚህ ወጣት ዲያቆናት በብፁዕ አቡነ ሣሙኤል እየተስተማሩና እየታዘዙ እሁድ በጥዋት መቅደሱን እያዘጋጁ ድንኳኑን እየተከሉ፣ ከአገልግሎት በኋላ እየነቀሉ ተሸክመው ከቦታ ቦታ እያዘዋወሩ ካነጹት ቤተክርስቲያን፣ በዕምነት አልባ ፖለቲከኞች፣ በጠባብ ብሔረተኞችና ጎጠኞች፣ በእበላባይ ሆዳሞችና ጊዜያዊ ጉልበተኞች አምላካቸውን ከሚያገለግሉብት፣ ከሚያወድሱበት መቅደስ ተገለሉ፡፡

           ይህ እርምጃ የሚገመገመው በተከታታይ ከተወሰዱ ተመሳሳይ እርምጃዎች ጋር በጋራ እንጂ ብቻውን በተናጠል ምንም ቤት አይመታም፡፡ በአብያተክርስቲያናትና በኦርቶዶክሳውያን ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ጦርነት ተከፍቷል፡፡ የሕዝቡን እይታ ያልያዘበት ምክንያት ምናልባትም እንደ ግራኝ መሐመድ ወረራ ከእምነቱ ውጭ የመጣ ስላልሆነና የሰው ህይወት ስላልተዋደቀበት ሊሆን ይችላል የሚል የራሴ ግምት አለኝ፡፡ ስፋቱና ጥልቀቱ ከዚያን ግዜው ከማነሱ በስተቀር በመጨረሻ ሊያደርስ የሚችለው ጥፋት ግን እያዘገመ የሚጓዝ እምነታችን ላይ እንደዘንዶ በመጠምጠም ላይ ያለ ነቀርሳ መሆኑን መጠራጠር እንደሰጎን እራስን አሸዋ ውስጥ ምቅበር ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ሳይውል ሳያደር በተለያዩ እስቴቶች ያሉ ለዚህ ጦርነት ሰለባ የሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ሕዝበ ከርስቲያን በሙሉ ሊዋጉት ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት ያለኝ፡፡

           እሰካሁን አልጠረጠራችሁ እንደሆን፣ ይህንን የሃይማኖት ጦርነት በፊታውራሪነት የሚመሩት ብፁዕ ሻለቃ መልከፄዴቅ  ናቸው፡፡ ጦርነቱ የተከፈተው በመጀመሪያ ከማስተማርና እራሳቸውን ለተሻለ የወንጌል አገልግሎት የበለጠ ለማጎልበት ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት ሲሯሯጡ ለራሳቸው ክብርንና ልዩ ስፍራን  ጠይቀው የማያውቁትን ወንጌላዊው አባ ገብረሥላሴ ጥበቡን ወንጌልን ከሚሰብኩበት አውደምሕረት በማስባረር ነበር፡፡ መቼም እውነትን መናገር፣ ለእውነት መቆም ወንጀል በሆነበት ቦታ ደፍሮ እውነትን መናገር ለእውነት መቆም ከመባረርና ክመሳደድ አልፎ የሕይወትም ዋጋ ጭምር ሊጠይቅ ይችላል፡፡ አባ ገብረሥላሴ የተሳደዱት ለእውነት መቆማቸው እንደጥፋት ተቆጥሮባቸው ነው፡፡ ዋናዋ ሰለባ የሆነችውና በመስቀል ላይ የተቸነከረችው ግን እውነት እራሷ ሆነች! አባ ገብረሥላሴ ግን ባላመኑ አረማውያን እጅ የወንጌላውያንን ፀጋ በክብር ተቀበሉ፡፡    

          በሻለቃ መልከፄዴቅ  የሚመራው ማለትም በደብረ ሃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ከቀድሞው ቦርድ ሊቀመንበር፣ ጎጠኛ ደጋፊዎቻቸው፣ የሲኖዶስ ድጋፍ ሰጪ ኮማንዶ ብርጌድ በአንድ ወገን እና በኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት ኦርቶዶከስውያን በሌላ ወገን ሆነው የተፈጠረውን አለመግባባት ለማርገብ በሠላሳ ሁለተኛው የሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ በተደረገው ውሳኔ መሠረት ሶስት አባላትን፤ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብን ከአትላንታ፣ ብፁእ አቡነ ዮሴፍን ከላስቬጋስ እና አባ ገበረሥላሴ ጥበቡን ከሲያትል፤  ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ቦታው መጥቶ ነበር፡፡ በዚህም ተልእኮው ቡድኑ መዕመናኑን በቡድንና በተናጠል፣ የአመራር አካላትን በቡድን፣ ሊቀመንበሩን በግል በማወያየት የራሱ ውሳኔ ላይ በመድረስ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ምርጫ ለማካሄድ ውሳኔ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ፍትህ የሚባል ቃል ለጆሯቸው እንግዳ የሆነባቸው ሊቀመንበር ምርጫው በፍትህ ከተካሄደ የፈለጉትን ማስመረጥ ስለማይችሉ ያላቸው ዕድል ሂደቱን ማሰናከል ብቻ መሆኑን ስለተረዱት ጎሮዶማኖቻቸውን ቀስቅሰው በቡድኑ አባላት ሕይወት ላይ ዛቻ ተላለፈባቸው፡፡ ሊቀመንበሩም ልትገደሉ ነውና ባስቸኳይ ወደ መጣችሁበት ጥፉ የሚሉ ሁለት ደብዳቤዎች ጻፉላቸው፡፡ ዛቻውንም እውነታ ለመስጠት ክጎሮዶማኖቹ አንዱ አንደኛው ሊቀጳጳስ መኝታ ቤት ገብቶ ሲዝትባቸው አሁንም ሆነ ወደፊት ቤቱ ከክርስትና ውጭ የሆነና ምንም ተስፋ የሌለው መሆኑን በመረዳት ይመስላል በማግስቱ ሁለም ሁሉንም ጥለውት ወደየመጡበት የተመለሱት፡፡ ፎካሪው እንግዲህ እስካሁን ከየትም ይሁን ከየት ካሳ አግኝቶ እንደ ሆነ ግን የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ባሳዩት ጠንካራ አቅዋም ነው እንግዲህ መነኩሴው አባ ገብረሥላሴ መስዋዕትነትን የከፈሉት፡፡

           ሁለተኛው የሻለቃው ሰለባ ሊሆኑ ተዶልቶባቸው የነበሩት  የሳንዲዬጎው መነኩሴ መምህር አባት ካህን አባ ቃለጽድቅ ነበሩ፡፡ ከቦርድ አባሎቻቸው ጋር ዶልተው በሳምንቱ እሑድ በሕዝብ ፊት አዋርደው ሊያባርሯቸው ያሰቧቸው መነኩሴ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ደህና ይሰንብቱ ብለው ከመቶ ዘጠናው ጤነኛ ምዕመን ተከትሏቸው ነጎዱ፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ እኒህ እብሪተኛ የአዋቂ አጥፊ አረጋዊ ሻለቃ የገነቡት በድቡሽት ላይ እነደሆነ የተከሰተላቸው፡፡ አንበሳ አጋጠማቸውና ተደቆሱ፡፡ እንግዲህ በተረፏቸው አስር ምዕመን $2 ሚሊዮን የሞርጌጅ ዕዳ ሲከፍሉ ለማየት በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡ ወይስ እዚህ ዲሲ የተዘጋጀችላቸው አንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ እየኖሩ በቋሚነት ውጊያውን ከዚህ ሊመሩት ይሆን? ወይም ቦልቲሞር ባለው አምባቸው ውስጥ መሽገው መታኮሱንም ይሞክሩት ይሆናል፡፡ አምባው እንኳን የሚረባም አይደል፣ ብቻ ይሞክሩት፡፡

                 ኦክላንድ ተቀደምኩ በሚል ቁጭት ዋሽንግተን ያለውን ሰባኬ ወንጌል እንደኔ እንዳትሆኑ ሳይቀድማችሁ ቅደሙት የሚል ምክር ለግሰው አስባረሩት፡፡ ለነገሩ በአንድ አሁን የአመኔታ ጉባኤ አባል በሆነ ዘማሪ  ግፊት ማንም ምዕመን ባልተቀበለው የሻለቃ መልከፄዴቅ ተሿሚ አስተዳዳሪ ደብተራ አስተባባሪነት በቀድሞው ሊቀመንበር ወሳኝነት በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የወንጌል ትምህርት ከታገደ ወደ ስድስት ወር ያህል ይጠጋዋል፡፡ መቼም አትስረቅ፣ አታመንዝር፣ የሰው ገንዘብ አትመኝ ወዘተ. የሚሉት ትዕዛዛት ካልተሻሩ በስተቀር የጌታ ወንጌል በኛ ቤተክርስቲያን እምብዛም ወዳጅ የምታፈራ አትመስልም፡፡ ከተጻፈች ወደ ሁለት ሺ ዓመት የሆናትን ወንጌል ለአንዳንዶች ተብሎ አሁን መቀየር ደሞ በቀላሉ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሰባኬ ወንጌሉ ሲያስተምር በቀጥታ እነሱን የተናገረ እየመሰላቸው ዐይናቸው ደም ይለብሳል፡፡ መቼም ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም አይደል ነገሩ፡፡ የወንድማቸው የመምህሩ መታገድ ያሳዘናቸው ዲያቆናት ጉዳዩ ክርስቲያናዊ እንዳልሆነ ተቃውሟቸውን ለማስመዝገብ ለታኅሳስ ገብርኤል ንግሥ ዕለት ሳይገኙ ቀሩ፡፡ ይህን ቀን አስበውበት የመረጡት ሳይሆን ቦርዱ ውሳኔውን ያስታወቀው በዓሉ ጥቂት ቀን ሲቀረው በመሆኑ ቀኑን የመረጠው እራሱ ቦርዱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መምህሩ ድርብ በደል እንደተፈፀመበትም ይነገራል፡፡ ክህነትን የመስጠት ሥልጣን የሊቀ ጳጳሱ ሆኖ ሳለ ከበታቻቸው ላለ ደብተራ አላስታወቁም በሚል ሰንካላ ምክንያት ሊሰጠው የነበረው የክህነት ሹመቱ እንዲታገድበት ሲደረግ እግረመንገዳቸውንም አንድ ሊቀጳጳስ በቤትክርስቲያን ውስጥ ሊኖረው የሚገባን በእግዚአብሔር የተቀባ ሥልጣን ፀረ ክርስቶሳውያን ሽረውታል፡፡ ያደቆነ ሠይጣን ሳያቀስስ አይለቅም ነውና ነገሩ ዲያቆናቱንም አብረው አሳደዷቸው፡፡ ይህ ትዕዛዝ የተላለፈው በቀጥታ ከጦር አዛዣቸው ከሻለቃ መልከፄዴቅ እንደሆነ ከራሳቸው ከአንደበታቸው የሰሙ ያረጋግጣሉ፡፡ ቅስናውን በተመለከተ ግን  በአንድ በእንግድነት ለረዥም ዓምታት ቤተክርስቲያን ውስጥ በኖሩ ጳጳስ ሁለት ግዜ ላገቡ ግለሰብ ቅስና ሲሰጡ ማንም ለማንም የነገረም ያስነገረም አልነበረም፡፡

           በዚህ ባለፈው እሑድ የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ ዕለት ለመብታቸው በቁርጠኝንት በመቆም ምዕመናን ትልቅ ጀብዱ ያካናወኑበት ታላቅ ቀን ሆኖ ውሏል፡፡ የአሜሪካን አገር ህገመንግሥት ቁልጭ አድርጎ የፈቀደውን የመጻፍ፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመናገር፣ የመቃወም መብት ሳይጠቅምበት በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለአመታት እንደከብት እየተነዳ የኖረው ሕዝብ በዚያን ዕለት ቁጣው ገንፍሎበት ታምቆ የኖረ ስሜቱን ያንፀባረቀበት የተቀደሰ ዕለት ነበር፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አሳሳቢ ሁኔታ ያሳሰባቸው ምዕምናን በፓትርያርኩ ፊት ቀርበው በሚገባ ችግራቸውን አሳውቀዋል፡፡ ታዲያ ተሳታፊዎቹ በብዛት እህቶቻችንና እናቶቻችን ሲሆኑ ጥቂት ጠንካራ ወንድሞቻችንም ታክለውበት ነበር፡፡  የወንዶቹ ቁጥር ሳሳ ማለቱ ግን አንድም ጉዳዩ አልገባቸውም ወይም ለእምነታቸው ብዙም ተጨናቂ አይደሉም ያሰኛል፡፡ ወንዱ ምን ነካው? መብቱን አያውቅም ወይስ ከቀይ ሽብሩ ሰቆቃ ገና አልባነነም?  አንዳንድ የቀይ ሽብር አራማጆች የነበሩትን በቅርብ የሚያውቃችውን ግለሰቦች በአካባቢው ሲያያቸው አሁንም ያባንነው ይሆን? እግዚአብሔር ዕምነታቸውን ያጽናላቸው፣ ተልእኳቸውን ይግለጽላቸው!

           ይህን አበሻ በይሉኝታ አፉን የያዘበት አኗኗር የጣማቸው ተመራጮች በቤተክርስቲያኒቱ አዲስ መተዳደሪያ ደንብ አሁንም የመዕመኑን አፍ ለማሸግ ሞክረዋል፡፡ ምንኛ ዝቅ ያለ አስተሳሰብ የተንሰራፋባቸው ሰዎች በመካከላችን እንዳሉ ሳስበው በውነት ይዘገንነኛል፡፡ የአንድ ቤተክርስቲያን የመተዳደሪያ ደንብ ከአሜሪካ ህገመንግስት በላይ ቀደምትነት ይኖረዋል ብሎ ማውራትና ማስወራት ትርፉ ትዝብት ላይ መውደቅ ነው፡፡

                 ልብ በሉ እንግዲህ ቤተክርስቲያን በውስጧ ምን ዓይነት ሰዎችን እንደያዘች፡፡ እኛጋ እንደምናየው የሚመሯት ከጦር አዝማች ሻለቃቸው ጀምሮ በተዋረድ እምነት የሌላቸው ፖለቲከኞች፣ የአገር ፍቅር የሌላቸው ጎጠኞች፣ ፍቅረ ነዋይ የተጠናወታቸው ስግብግቦች መሆናቸውን የተገነዘብን ይመስለኛል፡፡ እውነትንም እንደክርስቶስ በመስቀል ላይ የቸነከሯት እነዚሁ ሃይማኖተ ቢስ ከሀዲዎች ናቸው፡፡ ጥቂት ጎጠኞች ለአንድ ሙሉ ክፍለሀገር ስም መነሻ መሆናቸው ያሳዝነኛል፡፡

 

ወንድማችሁ ኃይለገብርኤል ታደገ

Posted in Uncategorized | 1 Comment

እርግማን አለብን?

ከቅኝ አገዛዝ ስር የወጡ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተለይ በአዲስነታችው ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸው እንደነበር ካነበብነውና ከሰማነው ግንዛቤ ሳንወስድ የቀረን አይመስልኝም፡፡ ቅኝ ገዢ አገር ለቆ ሲወጣ ያለ ምንም ተጠያቂነትና ያለምንም ጠያቂ ሲፈልጠው ሲቆርጠውና ሲግጠው የኖረውን አገር ሕዝብ እርስበርሱ እንዲባላ፣ ከጎረቤቱ እንዲናጭና ከቶም ሠላም እንዳይኖረው የማይጠፋ የማይስለመለም የመርዝ እሳት ለኩሶ አንቦግቡጎ ነበር የሚሰናበተው፡፡ ከዚያ በኋላማ ሰው ከጎረቤቱ፣ ወንድም ከወንድሙ፣ ከእህቱ፣ አንድ ዘር ከሌላው ዘር፣ ኩታ ገጠም አገሮች እርስ በርሳቸው መናከስ ነው፡፡ የሚንቦገቦገውን እሳት ያራግቡታል፡፡ የቅኝ ገዢ በግዛቱ ላይ እያለ ያገር ተወላጅ የውስጥ አጋር ባንዶች ከመሶቡ ላይ ትራፊውን እየተቀራመዱ የሚደልቡ ሁሉ ለቆ ሲወጣም የሥልጣን ኮርቻ ላይ ፊጥ ይላሉ፡፡ እነሆድ አምላኩ ትልቁ ምኞታቸው ባኗኗራቸው ለቆ የሄደውን ፈረንጅ ጌታቸውን መምሰል ነው፡፡

ቅኝ ገዢ ሕዝብን አባልቶ የሚሄደው የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ነበር፡፡ ሥልጣን በያዙት  የድሮ አሽከሮቹ አቅራቢነት ጥሬ ዕቃ በርካሽ ያገኛል፣ በሥልጣን ላይ በነበረበት ግዜ የሠራቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሎችና ዝርፊያዎች ይደበቁለታል፤ ባጭሩ የእጅ ኦዙር ቅኝ አገዛዝ ይሰፍናል፣ ይንሠራፋል፡፡  በውጭ ጨፍጫፊ ቦታ አገር በቀል ጨፍጫፊ ይተካል፣ ምስኪኑ ሕዝብ ግን በገባርነቱ እንዲቀጥል ይጠበቅበታል፣ ይበረታታል፡፡ አለበለዚያ ግን ይታፈናል ይታሠራል!

ቀደም ሲል ለረዥም ዓመታት ልክ እንደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በኣንድ ግለሰብ ይመራ የነበረው የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በአሁኑ ወቅት በዐይናችን እያየነው በፍጥነት የፖለቲካ ድርጅትነት ካባም ለመደረብ በቅቷል፡፡ በእውቅ በቀድሞው ሊቀመንበር ታማኝነታችው ተመስክሮላቸው የተመለመሉት አዲሶቹ የአመራር አባላትም፣ ጌታቸው ገነዘብንም ሆነ ንብረትን ጨምሮ ለምንም ነገር ተጠያቂነት እንዳይመጣባቸው በጽኑ እየታገሉላቸው ነው፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ታዲያ እውን እዚያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰው ታጣና ነው እቀድሞው ቦርድ ውስጥ በእውቅ ተመልምለው እንዲገቡ ተደርገው የነበሩት ሁለት የቦርድ አባላት እንደገና አዲሱ ቦርድ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉት? ለምን ተፈለጉ፣ ባላቸው ከፍተኛ የሥራ ልምድና ከፍተኛ እውቀት፣ ታማኝነት ወይስ ታዛዥነት? አሁን የቦርዱ ጸሀፊ የሆኑትስ ቢሆኑ በቀድው ሊቀመንበር የትምህርት ኮሚቴ መሪነት የተሾሙት አይደሉም? የተፈለጉትስ በቅድሞው ሊቀመንበር ቤተሰብ “መልቲካልቸራል ዩዝ ዴቬሎፕሜንት ኢንኮርፖሬትድ” በመባል የሚታወቀውን ከመንግስት ዳጎስ ያለ ገቢ በእርዳታ የሚያስገኘውን የሰመር ካምፕ ፕሮግራም ቀጣይነት ለማስረገጥ፣ ከምዕመን የተሰወረ ገቢውም በስውር እንዲቀጥል አይደለም? ፎቶግራፍ እየተነሱ እርዳታ የሚለመንባቸው ኅፃናትስ ቢሆኑ የምዕመናን ልጆች አይደሉም? ምዕመናን ልጆቻቸውን ቤተክርስቲያን የሚያመጡት እኮ ቤተክርስቲያን እየለመዱ እንዲያድጉላቸው እንጂ እንዲለመንባቸው አልነበረም፡፡ ምክትል ሊቀመንበሩስ ቢሆኑ እውነት ይሁንም ሀስት በአሁኑ ጊዜ የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው የሚባል ወሬ ቢነፍስም በመጀመሪያ የተቆናጠጡት በኒያው ሊቀመንበር መስተንግዶ ኮሚቴ ኃላፊነት ሹመት አልነበረም? እንግዲህ የተቀሩት ሰብጠርጠር ተደርገው የተሰገሰጉት የአመራር አባላት ደግሞ ተወርዋሪው የፈጥኖ ደራሽ ጦር ዘረኛም፣ ፖለቲከኛም፣ የጥቅም ተካፋይም አይደለንም ለማለት በተኩላ ሰውነታቸው ላይ ለማወናበጃ ጣል ያደረጉት የበግ ለምድ መሆኑ ነው፡፡

መቼም ደብረሃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤውም ሆነ አመኔታው ጉባኤው ቅንጣት ያህል የከርስትና እምነት የሌላቸው አትራፊ ነጋዲዎች፣ በህልም የሚጓዙ ሀምበርገር ስንቁ ከአሜሪካ ሁነው ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት የተነሱ ፖለቲክኞችና ቀንደኛ የጎጠኞች ጥርቅም ነው፡፡ የምሁር መሃይማኑንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ መቼም  አሁን እንደማየው ከዘመኑ ዶክትሬትና ማስትሬት ዲግሪ አለን ባዮች፣ በተፈጥሮ ልቦናውና የኑሮ ልምድ ባዳበረው እውቀቱ ተራው የሀገሬ ገበሬ ምንኛ ሊቅ ኖሯል በሉ?

ወራጁ ሊቀመንበር ለዚህ አይቀሬ ቀን ዝግጅት የጀመሩት ከረዥም ዓመታት በፊት እንደነበር አሁን ቤተክርስቲያኑ ከደረሰበት ውጥንቅጥ ውስጥ ሁነን ወደኋላ ለማየት ችለናል፡፡  እዩት እስቲ፤ ካለፈው ቦርድ ውስጥ በትክክል እኩሌታው ዘረኝነት አንገሽግሿቸው ቤቱን ጥለው ሲሄዱ  ትክክለኛ እርምጃ የሚሆውነ አዲስ ምርጫ ማካሄድ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ውክልና የሰጠው ለሁሉም አባላት እንጂ ለቀሩት ብቻ አልነበረም፡፡ እሳቸው ግን በሄዱት ቦታ አምስት ሰዎች መርጠው በቦታቸው ሞሉበት፡፡ አምስት ታዛዥ ጎሮዶማኖች ማለት ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ እንግዲህ በጀመሪያ ከጊዜያዊ ኮሚቴነት ያለምንም ምርጫ በዚያው ቋሚ ኮሚቴ ይሁኑልን በሚል የጎሮዶማኖች ሆሆታ ሥልጣኑን መሶባቸው እንዳደረጉት ሲቀጥሉ ለሁለተኛ ግዜ ደግሞ እንደገና በጎሮዶማኖቻቸው ቀስቃሽነት አዛውንት የፋርጣ ተወላጆች፣ በቅነሱ አነጋገር “አባቶች”፣ የቤተክርስቲያኑ ዕዳ ተከፍሎ እስኪያልቅ ይቀጥሉልን በሚል ማወናበድ አናፍተው ለዘለቄታው በዙፋናቸው ላይ ላማጽናት ታገሉ፡፡ አሁን ላይ ደርሰን ዐይናቸንን ከከፈትን በኋላ መውረዳቸው እርግጥ ሲሆን ሁለተኛ ፕላናቸውን ተረተሩት፡፡ የፋርጣ ማፊያ ቡድን እንደገና ለሥልጣን ጦርነት ትግል ክተት ሠራዊት ብሎ ተነሳ፡፡

ያሁኑ የፍጻሜው ጦርነት ነው ብለው ላሰቡት ግብግብ ከፍተኛ ዥግጅት ተደረገ፡፡ መቼም ለነሱ ቤተከርስቲያን ምን ግዜም ቢሆን የጥቅምና የጎጥ ቦታ ነው፡፡ ከአሥር አመታት በፊት  ከኢየሩሳሌም ቀጥረው ያመጧቸው የአጎታቸው ልጅ የሆኑት መሪጌታ የተገዙበትን ዋናውን የተንኮል ሥራችውን በደህና ግዜ ካደራጁት የፋርጣ ጦር መሪ ጋር በመሆን አገሩን ያተራምሱት ገቡ፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ አፋቸው በገንዘብ ከተሸበበ መዘምራን፣ ካንዳንድ ረብሻን ሲያልሙ አድርው ከሚውሉ ታክሲ ማህበራትን በክስ ከሚያምሱ ግለሰቦች፣ ከማርያም ቤተክርስቲያን ፈርጥጦ በመጣ የማይጸዳው አለቅላቂ የዘልዐለም ፖለቲከኛ አስመራጭ ኮሚቴ ሊቀመንበርነትና ከለንደን በተገዙ ሊቀጳጳስ በተጠናከረ አዲስ ምልምል የሚሊሺያ ጦር ጥቃት ተከፈተ፡፡ አሁን ትልቅ የሥልጣን ድርሻን የተጎናፃፈው የአርበኞች ግንባር የሕልም ጦር አዛዥም ቢሆኑ ባስመራጭ ኮሚቴነት ተሰልፈው ስለነበር በለስ ቀንቷቸው የራሳቸውን ተከታዮች  በቦርድ አባልነት አስሾልከው ለማስገባትም ቀንቷቸው ነበር፡፡ 

እኒሁ ጉደኛ ሊቀመንበር ቢተክርስቲያኑ ያለሕግ መኖርም መተዳደርም ስለማይችል ከተጠየቀው ምርጫ በፊት መተዳደሪያ ደንብ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ እሱንም እኔ አውጥቼ አመጣላችኋለሁ አሉና የሆነ ነገር ይዘው መጡ፡፡ ከአፋቸው ባይወጣም፣ አሥራ አምስት አመት  ሙሉ የመሩን በዘፈቀደ ያለምንም ሕግ እንዳሻቸው ሲሻቸው ከፍለው ሲሳቸው ነስተው፣ በሕዝብ ገንዘብ የዘማሪያንን፣ የጎሮዶማኖቻቸውና የአንዳንድ ጳጳሳትን ታማኝነት ገዝተው እንደሆነ ነገሩን፡፡ ትናንት የቤታቸውን ሞርጌጅ መክፈል ያቃታቸ ጎሮዶማኖች ዛሬ ጫን ያለ ቅድሚያ ክፍያ አድርገው ጫን ያለ ዋጋ የሚያወጡ መኪኖች ባለቤት የሆኑም አሉ፡፡ ማንም ሰው የማያውቀው ግን እሳቸው እራሳቸው ምን ሠርተው እንደሚኖሩ ዋና የገቢ ምንጫቸው ምን እንደሆነ ነው፡፡

አዲስ አወጣሁ ያሉትንም መተዳደሪያ ደንብም ከየትኛውም ሕግ ሆነ ከየትኛውም ልምድ ውጭ ሕዝቡ ለአንዲት ለሊት እንኳን እንዲያነበው ረቂቁ ሳይሰጠው በራሳቸው ሰብሳቢነት በራሳቸው አንባቢነት ሕዝቡ የሚያነቡትን አንቀፅ ለማብላላትም ሆነ እርስ በርሱ ለመወያየት ዕድል ሳይሰጠው አለፈ አለፈ ተብሎ በጎሮዶማኖቻቸው እየተፏጨ አፀደቁት፡፡ ይህን ሕግ ተብዬውን ለማስፀደቅ ፋርጤዎቹ ጎሮዶማኖቻቸውና የጎሮዶማኖቻቸው ጎሮዶማኖች ለመጮህም ሆን አንድን አንቀፅ ተቃውሞ የሚናገረውን አባል ለማንጓጠጥ አንድ ጥግ ነበር የተከማቹት፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የማፊያ ሥራ የሚጠበቀው ከእንደነሱ ዓይነት የእግዚአብሔርን ቤት ከሚዳፈሩ መናፍቃን ብቻ ነው ብል በፍጹም የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ምን ያድርጉ በአሁኑ ግዜ ሲኖዶሱን ካፈረሱት የነፍስ አባታቸው ከመልከፄዴቅ ዘፋርጣ ከዚህ ሌላ ምን ሊማሩ ኖሯል፡፡ ክፉ ለመዶለት፣ የተሠራን ለማፍረስ፣ የተሰበሰበን ለመበተን፣ ያማረን ለማበላሸት የተባ ምላስ የተሳለ ቁርጠኝነት ያላቸው መሆናቸውን በቤተክህነት ውስጥ ያለፈ በሙሉ ቢያውቀውም ከዚህ የጥፋት መልዕክተኝነታቸው ምን እንደሚያገኙበት የሚያውቁት ግን እራሳቸው ብቻ ናቸው፡፡ ታዲያ ዘመዶቻቸው ለምን የተለዩ ይሆናሉ ብለን አሰብን?

በዚህም የጥፋት መልዕክተኝነታቸው ነው ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ያለውን የግሌ የሚሉትን ቤተከርስቲያን የበተኑት፡፡ እጅግ በጣም የሚበዛው ምዕመን ጤንኛውን መምህር ተክትሎ ጤነኛ የወንጌልን ትምህርት ለመማር የሄደው ጥንቱኑ ያልነበራቸው ጤንነት በስተርጅና ከወዴት ያመጡታል በማለት ነው፡፡  ሲያትል ዋሽንግተን ታዋቂ የወንጌል መምህር የነበሩትን ትልቁን መነኩሴ አባ ገብረሥላሴ ጥበቡን ክመምህርነት ሥራቸው ያባረሩት ለምን እንደሆን አባራሪው እራሳቸው በውል የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ እብሪት ምን እውቀት ያሻዋል?

ወደ ዋናው ነጥቤ ልመልሳችሁና መተዳደሪያ ደንቡ እንደሆነ ሆኖ ከፀደቀ በኋላ አስመራጭ ኮሚቴውን ከጀርባ ባስቀመጧቸው ጀሌዎቻቸው አንድ በአንድ አስመረጡ፡፡ አንዱን አባል በተለይ እራሴ በሥልጣኔ ሰይሜዋለሁ ብለው አስገቡት፡፡ ከሳቸው ቃል  ዊልፊጥ ለማለት የሚችል አልነበም፡፡ ወይ የሰው ባለዕዳ መሆን! ያለሳቸው ፍቃድ ፉስም ግስም የለም! አንደኛው ደግሞ የፓርቲያቸውን አባላት ለቦርድ አባልነት ያበቁ በሜዳ ላይ የሞት ሽረት ትግል ላይ የተሰለፈ ጦር አዛዥ ናቸው፡፡ ከጦራቸው ተልይተው ከተማ መሀል ምን እንደሚሠሩ ግን አትጠይቁኝ፡፡ ምናልባት ዘመናዊ ጦር የሚመራው  ከኋላ ይሆን? ከማርያም ቤተከርስቲያን ስለተሰደዱት ያስመራጭ ኮሚቴ ሊቀመንበር ብዙ መነጋገር እንኳን አያስፈልግም፡፡ በደርግ ግዜ ከኢሓፓ ጀምሮ እስክ አብዪታዊ ሰደድ አምስቱም ፓርቲውች ውስጥ በአባልነት የተሳተፉ፣ በውያኔ መማክርት ሸንጎ ውስጥ አባልነት ያገለገሉ ቋሚ እምንት የሌላቸው የእርጎ ዝንብ ናቸው፡፡ አስመራጮቹን በተመለክተ ስለ አንዱ ነግሬያችሁ የነሱን ጉዳይ ላጠቃልላችሁ፡፡ ማንም መራጭ ስለማንኛውም ተመራጭ ተቃውሞ ማንሳት፣ መነጋገር፣ ጉድ ማውጣት በፍጹም እንደማይፈቀድ አስጠነቀቁን፡፡ ዋ! በሕግ እንጠይቃችኋለን አሉን፡፡ እህስ ስንል መብታችሁ መምረጥ ብቻ እንጂ መቃወምን አያካትትም ብለው የአሜሪካ ሕገመንግስት የሰጠንን የመናገርና የመቃወም መብታችንን በአንድ ደቂቃ ገፈውን አረፉት፡፡ እሳቸውም ሕዝብን አዋየሁ አላዋየሁ፣ ደሳለኝ ከፋኝ፣ ግራ ቀኝ ሳይሉ አንድ ወዳጃቸውን ለድጋሚ የቦርድ አባልነት አበቁ፡፡ እሰየው! ታዲያ ወዳጅ ለመቼ ነው?

እንግዲህ ሁሉም ተጠናቀቀና ቦርድና ሱፐር ቦርድ ሥራ ለመጀመር በቁ ማለት ነው፡፡ አዲሶቹ ባለሥልጣኖች ከተመረጡ ሶስት ወር ሊሆናቸው ምንም አልቀራቸውም፡፡ የድሮው ቦርድ ሲወርድ አዲስ ሲተካ አሥራ አምስት የተዳእፈነው ሂሳባችን ይመረመራል፣ ከሲዲ ሽያጭ፣ ለጣሪያ ማሠሪያ፣ ለከፉ ቀንም ተብሎ የተቀመጠው የድሮዎቹ የቦርድ አባላት የሚመሰክሩላቸው አካውንቶች ምን እንደዋጣቸው ሊታወቅ ነው ብለን ተስፋ አደረግን፡፡  የምናውቀውን  እናሳውቃችኋለን ያሉን አፈጮማ ሊቀመንበር የሚያውቁትንና የማያውቁትን ለይተን ማወቅ አልተቻለንም፡፡ በዚህን ያህል ግዜ ውስጥ ሂሳቡን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የማወቂያ በቂ ግዜ አግኝተዋል ባይ ነኝ፡፡ ሥራው ሮኬት ሳይንስ አይደለም እኮ!! የድሮውም አዲሱም ቦርዶች የአንድ ሳንቲም አንድ ገጽታ ናቸው የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ ምነው አይሆኑ? ማዕከሉ እኮ ያው ፋርጣ መሆኑ አይደል? ሁሉም እኮ ከመልክፄዴቅ ዘፋርጣ ጋር አንድም በጥቅም አንድም በጋብቻ አንዱም በሥጋ ዝምድና የተገናኙ አይድሉ? ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ!!! ከነሱ ፍትሕን በከንቱ ጠበቅን፡፡

 ገንዘብ፣ ገንዘብ አሉን፣ ስጡ፣ ስጡ አሉን፤ ከመነሻው ምዕምን እጁን የሰበሰበው እኮ ያለፈው የት እንደደረስ ሳናውቅ ተጨማሪ አንሰጥም ብሎ ነው፡፡ ታዲያ ምነው ስለዛ ፍንጭ ጠፋ? ብዙዎቻችን ከቤርሙዳ ትሪያን ግል ወጣን የሚል ተስፋችን ከንቱ ሊሆን የተቃረበ መሰለን፡፡ ጥረት አድርገው ካልተሳካላቸው ግልጽ አድርገው ለሕዝብ ማቅረብና የሕዝብን ውሳኔ ተግባራዊ  ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡  ሕዝብ የመረጣቸው ለአገልግሎት መሆኑን ሳየዘነጉ አገልግሎታቸውን ቁልጭ ብሎ በሚታይ ግልጽነት ሊያከናውኑ ይገባል፡፡ ድብብቆሽ ድሮም አልረባ አሁንም አያዋጣም፡፡ አገሪቱ ውስጥ ሕግ መኖሩን መዘንጋትም ደግ አይደለም፡፡

ገንዘብ መውጪያዋም መግቢያዋም ብዙ ነው፡፡ በተቻለ መጠን መውጪያዋን ማጥበብ መግቢያዋን ደግሞ ማስፋት ብልህነት ነው፡፡ ከዚህም አንዱ መንገድ በተለያየ ምክንያት አላግባብ ተበትነው የቀሩ ገንዘቦቸን ሲቻል በውዴታ ሳይቻል በሕግ አስገዳጀነት መሰብሰብ አያስነውርም፡፡ ነውሩ የሌላን መቀማት የራስ ያልሆነውን አዘናግቶ ማስቀረት ነው፡፡ ባለፈው ጽሁፌ ልገልጽላችሁ እንደሞከርኩት በመዘምራን አካባቢ ብዙ ብር ይንከባለላል፡፡ አንድ ተረት ትዝ አለኝ፤ አባቱ ይሁን እናቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ የሚለው ብሂል እውነት ካልሆነ በስተቀር ሞቅ ያለ የሲዲ ሽያጭ ገቢ ካለበት ዘማሪ እጅ ገንዘቡን አምጣ ማለት ለምን ተፈራ? ወይስ ተደምረው ለሚያደርጉት የስም ማጥፋትና በዚህም በዚያም ዘማሪያንን ዝም ለማሰኘት የተከፈላቸው የአገልግሎት ዋጋ መሆኑ ነው? ለሎቹ በጥሬ ገንዘብ ወስደው ያቀዘቀዙትስ ቢሆኑ ለምን ዝም ተባሉ፡፡ ሱቁም እኮ ቢሆን እጅግ ብዙ ገንዘብ ይገላበጥበታል፡፡ ለምን ቀዳዳ መድፈኛ ሥርዐት አይወጣለትም፡፡ እሱም ጎጆ መውጪያነት ካልተቸረ በስተቀር?

ይቅርታ አድርጉልኝና፣ አመኔታ ኮሚቴ ማለት ምንድነው? የሚታመን ኮሚቴ ማለት ነው? በምን፣ ለምን ስለሚታመን? በቦርድና በሕዝብ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር የሚያስታርቅ ችግሩን የሚፈታ አካል ነው ነበር ነው የተባልነው፡፡ አሁን ግን እንኳን ችግር ሊፈታ እራሱ ችግር፣ ተዝቆ የማያልቅ የችግር መንስኤ ሆነ፡፡

የአመኔታው ኮሚቴ ትርምስ መፍጠር፣ የቦርዱ ከሃይማኖት ርቆ ፖለቲካ ውስጥ መዘፈቅ፣ ከአሥር ዓመታት በላይ ደከምን ታክትን ሳይሉ ያገለገሉ እውቅ ዲያቆናትና ንጹህ መነኩሴ አባት በይሁዳዊ እጅ መከራ ሲቀበሉ፣ ዐርብና ቅዳሜን ዲሲ ዳንስ ቤት አድረው ከነ ሃንግኦቨራቸው አውድምሕረት ላይ ከበሮ መታን ብለው ሲውተረተሩ፣ መቅደስ ውስጥ እዩኝ እዩኝ በማለት እንደጎረምሳ የሚያገላምጣቸው አዛውንት ካህናት ሲደማመሩ እውን እርግማን የለብንም ትላላችሁ? እግዚአብሔር እንደተወን ግን እርግጠኛ ሁኑ!!! እግዚአብሔር ቸር ነውና ፊቱን ይመልስልን ይሆናል፣ በመጀመሪያ ግን ከኛ ብዙ ይጠበቃል፡፡

ወንድማችሁ ኃይለገብርኤል ታደገ

Posted in Uncategorized | 2 Comments

ከመቼው ለዚህ በቁ?

እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ይባላል፡፡ ባለፈው ጽሁፌ ያወሳኋችሁ የደብረ ሃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጉዳይ ቀስበቀስ ንጥር ብሎ እየወጣ እንደንጋት እየጠራ ከተፍ አለ፡፡ የካህናት የግል ምኞት፣ ጎጠኝነት፣ በሁለቱም በኩል ያሉ ፖለቲከኞች የተለያእዩ አጀንዳዎች፣ የቤተክርስቲያኑን ገቢ ለረዥም ጊዜ በመተዳደሪያነት የያዙት ግለሰቦች በአንድ የጥቅም ሜዳ ላይ መጋጠም ያመጣው መዘዝ ሲሆን ሌሎችም ምኑም ምኑም ሳይገባቸው እንደ እሳት እራት የተማገዱ የዋሀንም አሉበት፡፡ እስቲ ተውኔቶቹን በየፈርጁ እናጢናቸው፡፡
በዚህ ባለፈው ሰንበት የአመኔታው ኮሚቴ ሊቀመንበር ከአውደምሕረቱ ላይ ለመዕመኑ ንግግር አደረጉ፡፡ ንግግራቸው የቤተክርስቲያኑ አዲስ አምራር የተለያዩ ክፍሎቸ ስልጣንና ሃፊነትን አስመልክቶ እንደሚሆን ገለጹልን፡፡ ምርጫው አልቆ ተመራጮቹ ሥራውን ከተረከቡ ሁለት ወር አለፈው፣ ለያውስ ቢሆን የኮሚቴዎቹ የሥራ ድርሻ ሃላፊንትና ሥልጣን መተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ በግልጽ ተቀምጦ እያለ የሳቸው ለዚህ ጉዳይ መድረኩን መያዝ ምንም አልተዋጠልኝም፡፡ ጥርጣሬዬ እውነት ሆነ፤ ዋናው አጀንዳቸውን በመጨረሻ ብቅ አደረጉት፡፡
የገንዘብ ችግር ነው፡፡ ምዕመኑ የሙዳየምጽዋቱን ቅርጫት አይቶት እንደማያውቀው እንደቀላል ዕቃ ገርምሞት ያልፈዋል፡፡ ለሠላሳ ዓመት የተገባውን ሞርጌጅ በአሥራ አምስት ዓመት ከነወለዱ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ከፍሎ የጨረሰ ምዕመን ምነው ታዲያ አሁን የሚያፈሰውን ጣሪያ በአንድ መቶ ሺ ብር ማሠራት ተሳነው የሚለውን ጥያቄ ነበር የንግግራቸው ማዕከል አድርገው የተነሱት፡፡ የአመኔታው ኮሚቴ ሊቀመንበር የዘለሏቸው እውነታዎች አሉ፣ ያልተገንዘቧቸው እንኳን አይመስለኝም፡፡ ያኔ ዕዳውን የከፈለው ምዕመን ግማሹ አሁን የለም፡፡ አብዛኛው ምዕመን አመራር አካሉ ለራሱ እንዲመቸው የፈጠረው ፀረኢትዮጵያዊነት የዘረኝነት ጎዳና አሳዝኖት ቤተክርስቲያኑን ጥሎላቸው ከሄደ አመታት አስቆጠረ፡፡ የቀረው ደግሞ ከዛሬ ነገ ይሻሻላል፣ ጎጠኝነት በክርስቲያናዊ ወንድማማችንት ይተካል በሚል ተስፋ እጆቹን ወደ አምላኩ ዘርግቶ ተቀመጠ፡፡ የዝምታን መሣሪያ ታጠቀ፣ አፉም ዝም ኪሱም ዝግት እጁም እጥር አሉ፡፡ እብሪተኞች ከዚህ ቀደም ያላዩትና ሊሆን ይችላል ብለው በፍጹም ያልጠበቁት የዝምታ መሣሪያ ቢመዘዝባቸው ማርከሻው ግራ ገባቸው፡፡ በዚህም ላይ ደግሞ ሂሳብ ነክቶት ኦዲተር አልፎበት የማያውቀው አሥራ አምስት ዓመት ሙሉ የገፈገፍነው ገንዘብ እምን ደረሰ የሚለው ሹክሹክታ እያየለ ሲመጣ ጥያቄው የመብትም ጭምር እየሆነ መጣ፡፡
ከጊዜ ብዛት ተዘንግቷቸው ካልሆነ በቀር የአመኔታው ኮሚቴ ሊቀመንበር ለዚህ ችግር ከማንም በላይ ከፍተኛ አስተዋጾዖ ማድረጋቸውን ቤተክርስቲያኑን ገና ያለቀቅን በኢትዮጵያዊነታችን በፅኑ የምናምን ምዕመናን አሁንም አለን፡፡ ከምርጫ በኋላ በተመራጮች ስብሰባ ላይ ተገኝተው በጎ ምክር በመስጠት መልክ አሁን የወረዱትን ሊቀመንበር “በሀገር ውስጥም ሆን በውጭ ሀገር የረዥም ጊዜ የሥራ አመራር ልምድ ያካበቱ ጠንካራና ታማኝ ሰው መሆናችውን ስለሚያውቁ ግራም ቀኝም ሳትሉ እሳቸውን ሊቀመንበር ብታደርጉ ለሁሉም ይበጃል” በሚል መልክ ስላስተዋወቋቸው፣ የትልቅ ሰው ምክር በመስማትም ሆነ በአበሻ ይሉኝታ፣ ምክራቸውን ሥራ ላይ አዋሉት፡፡ ታድያ እሳቸውን ለዚያ ሹመት ሲያበቋችው ሹመቱ ኃላፊነትንም አስከትሎ እንድሚመጣ ግን ያሳወቋቸው አይመስልም፡፡ ሹመቱ ጎጆ መውጫህ ነው ካላሏቸው በስተቀር የሕዝብ ገንዘብማ መቆጠር መመዝገብ መመርምርና ለባለንብረቱ ሕዝብ መቅረብ መገለጽ እንዳለበት ለማወቅ የረዥም ግዜ ዓለም አቀፍ የሥራ ልምድ የሚያሻው ጥበብ አልነበረም፡፡ ቀና መንፈስና ለእግዚአብሔር ቤት መታመን ብቻ እንጂ!!!
“ውቃቢ የሚያስለቅቅ ቡና” አጠጥተናችሁ እንዴት ሙዳየምጽዋት ውስጥ አንድ ብር በቻ ትጥላላችሁ ላሉትም ቢሆን ምዕምኑ ውቃቢ ስለሌለበት ቡናቸው ሊቀርበት ይችላል፡፡ ውቃቢ ያለበትማ መንገዱ ወደ ቤተክርስቲያን አልነበረም፤ ተለውጦ ከሆነም ለውጡ ዘሎናል፣ እሰየው!! ያኔ የቤተክርስቲያኑን ዕዳ የከፈለውም ሆነ አሁን ያለው አዲስ ምዕመን አንድ፣ ሁለት፣ አስር፣ ሀያና ከተገኘ ከዚያም በላይ ብር የሚጥለው በገዛ ገንዘቡ ፈቅዶ ወዶ ለነፍስ ቢሆነኝ ብሎ እንጂ ማንንም ፈርቶ አልነበረም ወይም ለሚቀርብለት አንድ ሲኒ ቡናና ቁራሽ ዳቦ ተመጣጣኝ ክፍያ መሆኑን በሂሳብ አስልቶት አይደለም፡፡
አሁን በስተመጨረሻ መንታ መንገድ ላይ ቆመን አንድ ብር ሁለት ብር አወጣችሁ ብሎ አንጃግራንጃ ከመናገር ከመነሻው ስተው ያሳቱንን እርምጃ አሁን ያገኙትን ሃላፊነት ተጠቅመው እርምት ባደረጉልን! የአሥራ አምስት ዓመት ገቢ ወጪያችንን ለይተው እንዲያሳውቁን በመከሩልን!! የምዕመኑ ጥያቄ ሌላ ምንም ትርፍ ጭራም ሆነ አንገትም አላበቀለም፣ ፖለቲካም ጎጥም የለውም፡፡ ሂሳብ ያው ሂሳብ ነው፣ የሚደብቀው የሌለው ደግሞ አይደበቅም፡፡ ሽፍንፍኑ ለአንድነታችን ፍጹም አይበጅም፣ ግልጽነት ነፃ አውጪ ነው!!

መቼም ያለፈው እሑድ ዕለተ ተክለሃይማኖት ለአመኔታው ጉባኤ እራስን የማጋለጫ ቀን እንደነበር ምዕምን ሁሉ ይስማማበታል፡፡ የአመኔታ ጉባኤ አባል የሆኑት አዛውንት እናት፣ አውደምህረቱን ለዘለፋ ማዋላቸውን በሃያልነቱ እፈራዋለሁ ብዙ ተዓምራትን አይቼበታለሁ የሚሉት መላኩ ገብርኤልም ቢሆን የሚወድላቸው አይመስለኝም፤ እከሌን ስደቡልኝ እክሌን አወድሱልኝ የሚል ውክልና የሰጣቸው ደግሞ አይመስለኝም፡፡ ምን አጥቶ? ምን ተስኖት? አለመታደል ነው እንጂ ሰው ለምን ደህና ለበስክ፣ ለምን ደህና ቤት ኖርክ ተብሎ ይወቀሳል? ሰው ሁሉ እኮ የሚለፋው ሁለትም ሶስትም ሥራ የሚያራውጠው አገሩ ጥሎ ከመጣው ኑሮ በተሻለ ሁኔታ ለመኖር ሲሆን ቢቻለው እዚያ የቀረውን ወገኑንም ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍም እኮ ነው፡፡ “አፍንጫ ሲመታ ዐይን ያለቅሳል” እንድሆን እንጂ ከልብ የመነጭ መቆርቆር ቢሆንማ የቤተከርስቲያኑን ገንዘብ ተበድራችሁ ያልከፈላችሁ፣ ንብረቱን ሽጣችሁ ገንዘቡን ያላስገባችሁ ክፈሉ ነበር መልእክታቸው መሆን የነበረበት፡፡ አመልካች ጣቱን ሌላው ላይ የቀሰረ ሰው የቀሩት ሶስቱ ጣቶቹ ደግሞ ባንፃሩ ወደ እራሱ መቀሰራቸውን ልብ ለማለት ትህትናንና የልብ መሰበርን ይጠይቃል፡፡ ሕዝብ ገንዘብ አልሰጥም አለ ተብሎ በአድመኝነት ይወነጀላል፡፡ ቢሰጥም ቢነሳም በራሱ ገንዘብ የሚያዝብት የለፋበት ባለቤቱ እራሱ እንጂ አመኔታ ጉባኤ አይደለም፡፡ የሰው መብት የተከበረበት አገር ነውና፣ በለው በለው ያዘው ያዘው በማለት ደብድቦ ወይም አስፈራርቶ መቀማት ደግሞ በሕግ ያስጠይቃል፡፡
ቤተክርስቲያኒቱ የሁለት ተቃራኒ ወገን ፖለቲካ ቡድኖች ስውር መናቆሪያም ሆናለች፡፡ በአንድ በኩል ወያኔን እንዋጋለን ባዮች፣ ስናዝንና ሆድ ሲብሰን መጽናኛችንን፣ ስንደስት ማመስገኛችንን የዕምነታችን ማዕከል ቤታችንን እቺኑ እፍኝ የማትሞላ እዚህ ግቢ የማይሏት ገቢያችንን በምን ዘዴ ለስንቅና ትጥቅ ማደራጃ ለመሣሪያ መግዣ ሊያብቃቋት እንዳሰቡ ለራሳቸውም የተገለፀላችው አይመስለኝም፡፡ ሌላ ማዕከል ሌላ ገቢ ቢያፈላልጉ ላያጡ ይችላሉና እይታቸውን ወደ ሌላ ቢቀይሱ ዕድላቸው ቀና ትልላቸው ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ ግን ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብለው ጫካውን በረሃውን ቢላመዱት ትንሽ ጎናቸው ደንደን ይልላቸው ነበር፡፡
በሌላው ወገን ደግሞ አንዱ ሲወድቅ ወደሌላው ተገልብጦ የሁለት መንግሥት ካድሬ ሆኖ ባገለገለ ግለሰብ የሚመራ ቡድን ነው፡፡ በሕዝብ ያልተመረጠ፣ በሕዝብ ውክልና ያልተሰጠው የሥልጣን ማዕክል መስርቶ ሲኖዶሱንም ቦርዱንም የሚያምስ ሕዝቡንም እርስ በርሱ በማባላት ቤቱን ለመበተን የተቃረበ የዲያብሎስ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ነው፡፡ እነዚህ የጥፋት መልዕክተኞች ቅዳሴ ሳይገቡ አስቅድሶ የሚወጣውን ምዕምን በየኮሪዶሩ እየጠበቁ ያጠምዱታል የረጋውን መንፈሱን በነገር ይበርዙበታል፣ ክፉ ይመክሩታል፣ ያስቱታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ቤቱን የናጠው የጎጠኝነት ጠማማ ምክር የተቆላው፣ የተፈጨው፣ የተቦካውና የተጋገረው በዚሁ ቡድን አባላት በአንደኛው መኖሪያ ቤት ውስጥ በተዶለተ ያልተቀደሰ ስብሰባ ነበር፡፡ ይህ ቡድን በመጀመሪያ ስብሰባው ላይ የቀድሞውን ሊቀመንበር በተደጋጋሚ በሥልጣናቸው ላይ ያለምንም ተቃውሞ እንዲንሰራፉ መሠረት የጣለው በዚህ ሁኔታ አስመራጭ ኮሚቴውንና የአመራር አባላቱን ዝርዝር በቅድሚያ ወስኖ ውጤቱንም በትጋት አስፈፅሟል፡፡ አንድ ሞኝ የተከለውን ሺህ ብልህ አይነቅለውም ሆነና ያንን ለመንቀል ስንት ጥፋት ተፈጸመ፡፡ የጥፋቱን ጥልቀትና ስፋትም ቢሆን ግዜ ያወጣው እንድሆን እንጂ ለግዜው ለሁላችንም የተከሰተልን አልመሰለኝም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የብልጠት ጎዳና አንድ ቀን ይጋለጣል ብለው አለመገመታቸው የመዕምኑን ዝምታና ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳላዋቂነት መቁጠራቸው ነው የሚል የራሴ ግምት አለኝ፡፡ የቡድኑ አካሄድ በቤተክርስቲያኒቱና በመዕመኑ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችንት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጥፋት የተገነዘቡ አንዳንድ ባለህሊናዎች ለሚያነሱት ጥያቄ በቡድኑ መሪ የሚሰጣቸው ስልታዊ ምላሽ፣ “ምነው እኛው በኛው እንዴት እንዲህ እንባባላለን? ባይሆን ሌላ ሳይሰማ እንውቃቀስ እንጂ” የሚል ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከሰዕሉ ውጭ የሚያደርግ የተለመደው፣ ሁሉም ያወቀው ጎጠኛ ጥቅስ ነው፡፡
እዚህ ላይ በጣም የሚገርመኝ በአንድ ፊቱም የሚያሳዝነኝ ነገር በመካሄድ ላይ ያለውን ውዝግብ ከጥቂት ወራት በፊት በሽምግልና መልክ ገብተውበት የነበሩት የሬዲዮና የቴሊቪዥን ሰዎቻችንን የበላቸው ጅብ አልጮህ ማለቱ ብቻ ነው፡፡የነሱም ድምፅ ተበላ እንዴ? ጉዳዩን ከስር ከመሠረቱ አጥንተው ችግሩ እምን ላይ፣ እማን ላይ እንደሆነ በትነው ከተረዱ በኋላ መፍትሄ ለማስገኘትም ከፍተኛ ጥረት አድርገው እንደነበርም ብዙዎቻችን እናውቃለን፤ ጥረታችው ለምን ፍሬ እንዳላፈራም እናውቃለን፤ እንደምናውቅ እነሱም ያውቃሉ፡፡ እንግዲህ ተዋውቀናውል ማለት ነው፡፡
ይሄን ያህል ካወቁ ታዲያ ምን ሆኑና ነው ችግሩን ለሕዝብ ያላወጡት? መጠኑና ዐይነቱ ይለያይ እንጂ በኢትዮጵያውያን አብያተክርስቲያናት ሁሉ ችግር እንዳለ ያደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ቸግሩን ለሕዝብ ውይይት ማቅረብ ከኔ ወዲያ ገንዘብ ያዥ፣ ከኔ ወዲያ ሊቀመንበር ከንቱ፣ ከንቱ ውዕቱ፣ ባዮችን በማሳፈር መስመር ሊያስይዛቸው ይችል እንደነበር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ወይስ፣ ወይስ እነሱም እኛውጋ እንዳሉት ወንድሞች እጄን በጄ ሆነባቸው? ዘረኝነት፣ ሙሰኝነት፣ ጋዳፊነት አዲስ አበባ ብቻ ነው ያለው የሚል እምነት ካላቸውም ተሳስተዋል፡፡ ፍርዳቸው ሁለት ዓይነት ሚዛን እንዳይኖረው እራሳቸውን መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ ትግል ከራስ ይጀምራል፡፡ ለዓላማችሁ ታማኝ ሁኑ! ወርቅ ልሳናችሁ አይዘጋ! በእውነት በሃቅ አብቡ!
አዲሱ የአመራር አካል፣ አመኔታውም፣ ሰበካ ጉባኤውም ሆነ ቁጥጥር ኮሚቴው ከሕዝብ ጋር ሊኖረው የሚችለውን ዝምድና ከመነሻው ጤናማ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ተአማኒነትን ያስገኝለታል፣ ሥራውን ያቃናለታል ውጤቱም አመርቂ ይሆናል፡፡ ለአመራር መመረጥ ማለት ለአደራ፣ ለአገልግሎት መመረጥ እንጂ ለሥልጣን ወይም ለፈላጭ ቆራጭነት ጉልት መተከል አለመሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ትህትናን ገንዘባችሁ አድርጉ ለመታዘዝ የፈጠናችሁ ለማዘዝ የማትሽቀዳደሙ ሁኑ፡፡ በድርጅታዊ መዋቅሩ መሠረት የዕለት ተዕለት ተግባር የማከናወኑ ሃላፊነት የሰበካ ጉባኤው ሆኖ ሳለ፣ አመኔታ ጉባኤው ቀደም ቀደም ማለቱን አልወደድኩለትም፡፡ አውድምሕረት ላይ ቆሞ ምዕመንን ማንጓጠጥ ትንሽነት እኒጂ ትልቅነት አይደለም የትልቅ ትንሽ ከመሆን ደግሞ ሁላችንንም እግዚአብሔር ይሰውረን!!!

ወንድማችሁ ኃይለገብርኤል ታደገ

Posted in Uncategorized | 1 Comment

የግሌ ሲኖዶስ

የግሌ ሲኖዶስ!

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  ከማንኛውም የኢትዮጵያ የክርስቲያን ዕምንት ተቋማት በሙሉ በተለየ ሆኔታ በሁለት ሲኖዶሶች የሚወከል የዕምነት ማዕከል ሲሆን የአንዱ ውክልና በሀገር ውስጥ የሌላው ደግሞ በባሕር ማዶ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡  ታዲያ የባህር ማዶው ሲኖዶስ የተቋቋመው የአገር ውስጡን ተቃውሞ ስለነበር ሁለቱ ሲኖዶሶች ዓይን ለዓይን የማይተያዩ ጠላቶች ናቸው፡

በስደተኛው ሲኖዶስ አባባል ፓትርያርክ በሕይወት እያለ በላዩ ላይ ሌላ አይሾምበትም የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ የዘረኝነትም ጉዳይ ትልቅ ሥፍራን የያዘ ነጥብ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም አዲስ ተሿሚ ምንጊዜም ቢሆን የራሱን የቅርብ ታማኞች ይዞ ስለሚመጣ የቀድሞዎቹ የቤተክህነት መሪዎች ውሎ አድሮ ቦታቸውን መነጠቃቸውም አይቀሬ መሆኑንም ከወዲሁ የተረዱት ይመስላል፡፡ በተለይም የስደተኛው ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው  የዕድሜ ባለፀጋ ሊቀጳጳስ ቀደም ሲልም ለአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት በአማካሪነትም ያገለገሉ ስለነበሩ የሥልጣን መንጠላጠያ መሰላሏንና መሽሎክሎኪያ ቀዳዳዋን፤ ሥልጣን ስትመጣ መጣፈጧን ስትታጣ ምሬቷን ጠንቅቀው የሚያውቁ  ስለነበሩ ከሃይማኖት አባትነቱ ይልቅ የፖለቲካውን የረቀቀ ፍትጊያ ይበልጥ ያጣጥሙ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡ ፖለቲከኝነት በራሱ ነውር ባይሆንም ከሃይማኖት አባትነት ጋር ግን በፍጹም እጅ ለእጅ ተያይዞ አይሄድም፡፡ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ደግሞ ለራሱ ለእግዚአበሄር ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለሁለት ጌታ ሊገብሩ የሞከሩ ግዜ ነው ከሁለቱም ሳይሆኑ የቀሩት፡፡

                አንድ የሚሠራውን የሚያውቅ ተቃዋሚ ድርጅት ሌላው ቢቀር በምንም ዓይነት ቢሆን  ተቃውሞት የተነሳውን ድርጅት የጥፋት ጎዳና መከተል በራሱ የዝቅጠቱ መነሻ ምልክት ነው፡፡ የሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ  ከምንምና ክማንም በላይ ዓይናቸው ሥልጣናቸውን ማጠናከሩ ላይ ስለነበር በአራት ነባር ሊቀጳጳሳት ጥንስስነት ዘጠኝ ጳጳሳትን በመሾም ሲኖዶሱን ከመሠረቱና ካስመሠረቱ በኋላ ከዋሽንግተን ዲሲ ቅዱስ ገብርኤልና ክቦልቲሞር ቤተክርሰቲያናት ታማኝ ወገኖቻቸውን መልምለው ክቃለ አዋዲው ውጭ “የሲኖዶስ ድጋፍ ሰጪ” በሚል መጠሪያ አንድ ልዩ ፈጥኖ ደራሽ ተወርዋሪ ጦር ፈጥረዋል፡፡ ይህም ለበርካታ ወጣቶች ሕይወት ህልፈት ተጠያቂ የሆነው የቀድሞ  የቀይ ሽብር ኮሚቴ አባላትን፣ግልብጥ ካቶሊኮችንና ቤተክርስቲያን ውስጥ አንዲት ቀን እንኳን ገብተው አስቀድሰው የማያውቁ ከእግዚአብሔር ካሳ የማይገባቸው ዕምነት አልባ ፖለቲከኞን ያካተተ ሽብር ፈጣሪ የሚሲዮን ጦር በመሠረቱ  የተመለመለው ከደብረታቦር አውራጃ ባብላጫም ፋርጣ በመባል ከምትታወቅ አንዲት ወረዳና አንዳንድ ጀምበር ከጠለቀባቸው ወዶ ገባዎች መሃል መሆኑ ያደባባይ ሚስጥር ክሆነ ሰንብቷል፡፡ መቼም እንደሳቸው ካለ አረጋዊ የኃይማኖት አባት ምዕመንን በዘር መለየት የማይጠበቅ ቢሆንም ምንም ቢሆን ካገር ልጅ በላይ የሚታመን የለም፣ ሌላው ምን ያረጋል፣ በሚል እሳቤ የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ ከጥንት ባሕሪያቸውን የሚያውቁ በሕይወት ያሉ ምስክሮች ሞልተዋል፡፡

በዚህ ዓይነት ጠባብ ብሔረተኝነት የተወጣጠረ የበላይ አካል በስሩ ምን ዓይነት አብያተክርስቲያናት እንዳቀፈ ወይም እንዳካተተ ለማየት እንዲረዳ ከሩቅም ከቅርብም ከውጭም ከውስጥም ንጹሕ ህሊና ባላቸው ኢትዮጵያውያን አነሳሽነት አንድ በውል ያጠናሁትን ቤተክርስቲያን ጉዳይ በተምሳሌነት ላውጋችሁ፡፡

                በኖርዝ ኢስት ዋሽንግትን ዲሲ ክፍለከተማ ብላደንስበርግ መንገድ ላይ የሚገኘውን ደብረኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን የምታውቁት መቼም ታውቁታላችሁ፡፡ ቤተክርስቲያኑን ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት በቦርድ ሊቀመንበርነት የመሩት ግለሰብ  የመጡት ከፍ ብለው ከተጠቀሱት የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ጋር ካንድ ወረዳ በመሆኑ ከነፍስ አባታቸው ብዙ ትምህርት ሳያገኙ አልቀሩም ብዬ አስባለሁ፡፡ በመሠረቱ ጎሮዶማኖቻቸው በሃርቫርድ ምሩቅነታቸው የሚያወድሷቸው እኒህ ሊቀመንበር ለሥልጣን ባላቸው ልዩ ጥም ከነፍስ አባታቸው የሚተናነሱ ባይሆኑም የእነዚህ ሁለቱ ሰዎች ለሥልጣን ሟችነታቸው ግብ ግን እየቅል ነው፡፡

                እኒህ  በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትና ለስለላ ድርጅቱም  ጭምር በሰጡት አገልግሎት ታዋቂነትን ያተረፉት ሊቀጳጳስ ከምንም በላይ ትልቅ ነኝ ብሎ መኮፈስንና ከንቱ ውዳሴን ከልክ ባላይ ስለሚወዱ ይህን ነባር ሱሳቸውን የሚያረካላቸው ማንም  ብልጣብልጥ አምታታው በከተማ እንደ ህጻን ልጅ እጃቸውን እየጎተተ  ሊጫወትባቸው እንደሚችል በተዳጋጋሚ ታይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት የቅዱስ ገበርኤል ቤተክርስቲያን ሊቀመንበርነታቸውን ከአሥራ አምስት ዓምታት በኋላ  በብርቱ ግብግብ ያስረክቡት ግለሰብ ይህን ሱስ በትክክል ስለተረዱላቸው ከንቱ ውዳሴውን ጎንበስ ቀና፣ እጥፍ ዘርጋ በማለት ያለምንም ገደብ ያረኩላቸዋል፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በተንኮል፣ ምዕመንን ክምዕመን፣ ካህንን ክካህን በማጋጨት የሚታወቁትና በሲኦል ደቼ ያቦኩት የመርዝ  እርሿቸውን በመቅደስ ውስጥ በጥብጠው የረጩትን ተስፋ የሌላችው ተስፈኛ በአስተዳዳሪነት ለማስሾም የተጠቀሙበት ዘዴ ያንኑ መከረኛ የፋርጣ ተወላጅነታቸውንና ሿሚው የሚወዱትን ከንቱ ውዳሴ በማቅረብ ነበር፡፡

ሊቀመንበሩን እንኳን መቼም አምላክ መሐሪ ነውና ይምራቸው እንደሁ እንጂ ሥራቸው እንኳን ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚያደርሳቸው አይመስልም፡፡ ሁሉንም ይወዱታል፣ በተለይም  ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ካለው፡፡ የሕይወታቸውን መስመር ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል በሚል ፍልስፍና ላይ የመሠረቱ ስለሆነ በዚህ በመሸበት ዕድሜያቸው ይለወጣሉ ብሎ ማሰብ ከንቱ ሕልም ይሆናል፡፡ አንዲት ትንሽ ቤተክርስቲያን በቅጡ መምራት ተስኗቸው የሚደነባበሩ ሰው በጎሮዶማኖቻቸው አፍ ጋሼ ጋሼ ተብሎ መጠራትን ፣ አገር ይመራሉ ተብሎ መሞካሸቱንና ከንቱ ውዳሴን እንደ እውነት ይቀበሉታል፡፡ ጭንቅላታቸውን ደመና ውሰጥ ክተው በፍጥነት በመንደርደር ላይ ያለውን የውርደታቸውን ድግሰና የታምቡር ድለቃ ክማየት የጋረዳቸውም ይሄው ከንቱ ውዳሴን አምነው መቀበላቸው ነው፡፡

                አሁን በግልጽ እየታየ እንደመጣው ሁን ተብሎ የተያዘው አማራጭ ግን ክሕግ በላይ በመሆን ለማንም ተጠያቂነት የለብኝም ወደሚል ወለል የለሽ አዘቅጥ እየወረዱ ይመስላል፡፡ ቀደም ብሎ ከላይ እንደተመለከትነው እሳቸውም የግል ጠባቂ ልዩ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ከዚያችው ከጎጣቸው ቀደም ብለው ማደራጀታቸው የቁርጡ ለት ቀኑን ጠብቆ ተከሰተ፡፡ ይህ ስመጥፉ ይሉኝታቢስ የቅጥረኞች ጦር በእውነተኛ የእግዚአብሔር መንገድ የሚጓዙ ምዕመናንን ጥሩ ስም የማጉደፍ ፀያፍ ተግባር ላይ በመሰማራት ሰንካላ አስተዳደጋቸውን ፍንትው አድርገው ፀሐይ ላይ አስጥተውታል፡፡ ሕዝብ ሊቀመንበሩ እንዲወርዱ ሲጠይቅ እንዲቆዩ በመምከርና ሌሎች መሰሎቻቸውን በጎጥ በማደራጀት ጥያቄውን ለመቀልበስ መታገል፣ ሂሳባቸው ይመርመር የሚል ጥያቄ ሲነሳማ ጭራሽ እንደ አዶከብሬ የሚያስጓራቸው ለጉድ ያስቀመጣቸው ጉዶች ናቸው፡፡

                ከጎጠኞቹ ሌላ ለዚህ ተግባር የተሰለፉት ምልምል የወሬ ኮማንዶዎች ተአማኒነታቸው የተገዛው አነሰም በዛ በገንዘብና በልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም ነው፡፡ ከንዋየ ቅዱሳት መሸጫ ሱቅ ያለ ምንም ቁጥጥርና የዋጋ ተመን ዕቃ አስገብታ ምን ያህል እንዳቀረበች እንኳን ሳይታወቅ ቸርችራ ከምትጨርሰው ወይዘሪት ጀምሮ፣ ከነልጆቿ ወደ ኢትዮጵያ ደርሶ መልስ ያይሮፕላን ቲኬት የሚገዛላትን እመቤት፣ ልዩ ብድር የተሰጠውን ወጣት የልጆች አባት፣ ለቤተክርስቲያኑ ገቢ ለማስገኘት ታስቦ እንዲሸጥ በአደራ የተስጠውን ዲቪዲ ሽጦ በኪሱ የከተተውን የመሳሰሉት የሥርአቱ ግንባር ቀደም አጥፍቶ ጠፊ ወንበዴዎች ቋሚ ምሳሌዎቸ ናችው፡፡ በርዳታ የሚመጣ ዕቃ ተሽጥ ከሚገኘው ገቢ የሚቃመሱትም ቢሆኑ የበሉት ሆዳቸውን እየቆረጣቸው ምርመራን ለማጨናገፍ በሚደረገው ንቅናቄ በመሳተፍ ለበሉበት እየጮሁ ናቸው::

                መቼም ገደብ የሌለው ሥልጣን የሚሠሩትን ያሳጣ የል፤ ሊቀመንበሩ በአንድ ወቅት ሊቀጳጳስ አንስቼ በሌላ ሊቀጳጳስ እተካለሁ ብለው ተነስተው ነበር፡፡የት የተቀበሉት ክህነት ለዚህ ክብር እንዳበቃቸው ባላውቅም፣ ምናልባት እሱም በሚስጥር በመንደር ልጅነት መታደል ጀምሮ እንደሆን የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ለማንኛውም ላለፉት አሥራ ስምንት ዐመታት ረሃብን ሳይቀር በብዙ ችግርና በብዙ መክራ ውስጥ ያለፉትን ሊቀጳጳስ፣ ቁምስቅላቸውን ሲያሳዩአቸው የኖሩት አልበቃ ብሏቸው እሳቸውን አባረው በቦታቸው ሌላ ለመተካት የማይታክት የማይጠግብ ዐይናችውን ወደ እንግሊዝ አገር አሻገሩት፡፡ከሃያ ዐመታት በላይ እንግሊዝ አገር ሲኖሩ ቢያንስ አስር ሰው እንኳን አሰባስበው ለስማቸው መጠሪያ አንዲት ትንሽ ቤተክርስቲያን መመሥረት ያቃታቸው፣ ከሰው ተስማምተው መኖር ያልቻሉ ሊቀጳጳስ ከባሕር ማዶ ለማስመጣት በቁ፡፡ በማስመጣት ብቻ አላበቁም። ግሪን ካርድ አስወጥተው ድርጎ መድበው ቤት አደላድለው ከመንግስት የሚገኘውን ጥቅማጥቅም አስከብረው የሁለት መንግስት ተጠቃሚ ለመሆንም አበቋቸው፡፡ ይገርማል፣ የዚችን ዐለም ከንቱነት መነኩሴውም ሳይቀር ሁሉም ዘንግቶታል  ልበል? የነገው ቀን ለሳቸው ምን ይዞ እንደሚመጣ ሳያውቁ ወንድማቸው ላባቸውን ያፈሰሱበትን፣ አበሳ ያዩበትን ቤተክርስቲያን ለመቀማት ከዋሾ ፖለቲክኞች ጋር ተባብረው ወንድማቸውን ለማይዘልቅ  ክብር ለሠላሳ ብር ሽጠው አረፉት፡፡ ነፍሳቸውን ይማራቸውና፣ በመኪና አደጋ ሕይወታቸ ያለፈው ጥሩ ክርስቲያን የሁሉ አባት የነበሩት የጥንቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳሰ ስም ከህልፈታቸው በኋላ በግብርም በዕምነትም ለማይመጥናቸው ሰው ተላለፈ፡፡

                የክፉዎች ሥራ ሲያልቅ አያምር ነውና ከላይ ከፍ ብሎ የጠቀስኩላችሁ “የሲኖዱሱ ድጋፍ ሰጪ” ተብዬው ቡድን ከቦልቲሞር ከየአምባቸው ተሰብስበው በመጡ ካህናትና ሌሎች ፖልቲከኛ ነን ባይ ሕልመኞች ታጅቦ ለጊዜው የመጨረሻ እርምጃ አድርገው የወሰዱት በ ኦሃዮ ሠላሳ ሁለተኛውን የስደተኛው ሲኖዶስ ግማሽ ዓመታዊ ስብሰባ ረግጦ በመግባት ስብሰባውን መበጥበጥ ሆነ፡፡ የኦሃዮው የሲኖዶስ ስብሰባ ከጳጳሳት፣ ከመነኮሳትና ከካህናት በስተቀር ለሌላው ዝግ ሆኖ ሳለ እነዚህ እምነተቢስ ደፋሮች በማን ትብብር በሩንስ ለመርገጥ በቁ? መቼም ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው ይባል የለ፣ የሲኖዶሱ ዋና ጸሃፊ ከነዚሁ ኢትዮጵያዊነትንም ሆነ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ከማያውቁ  ፖለቲከኞች ጋር ክመኖሪያቸው ከሳን ሆዜ ወደ ቦልቲሞር ከተማ የስድስት ሰዓት በረራ አድርገው የሴራው ስብሰባ ተካፋይ ሆነው እንድነበር ተሰማ፡፡ እንግዲህ በዚህ መንገድ ነበር ለሶስት ቀናት በተካሄደው የሃይማኖ አባቶች ስብሰባ ላይ አባቶቹ አፋቸው ተለጉሞ ምንም ቃል ትንፍሽ ሳይሉ የውሳኔ ሃሳብም ሆነ ቃለጉባኤ ሳይቀርብ  እንደሚሸለት በግ በገዛ ስብሰባቸው ተመልካች ሆነው የተመለሱት፡፡ ስብሰባውን ተካፍለው የተመለሱት የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ስለስብሰባው ለምዕናን ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ስብሰባው በሠላምና በወንድማማችነት መንፈስ  መፈጸሙን የሀሰት ብሥራት ሲያበሥሩ  እራሳቸው ያለሟቸውን  ነጥቦች በስብሰባው ላይ የተወሰኑ በማስመሰል አውደምሕረት ላይ ቆመው ጉድ እየተባለ  ዐይናቸውን በጨው አጠበው  ያለህፍረት አነበነቡ፡፡ ከወጥ ቤት ሃላፊነት ወደ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበርነት ዕድገት ያገኙት እኒሁ ሰው ላስሾማቸው ቡድን ታማኘነታቸውን በሚገባ ለማስረገጥ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይመስላል፡፡

                የአመራር ለውጥ ጥያቄ በሕዝብ ዘንድ መንሳፈፍ ከጀመረብት ግዜ አንስቶ ይህ የሲኖዶሱ ስብሰባ እስተካሄደብት እስካሁኑ ግዜ ድረስ ቢያንስ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ክብሩ ይስፋና በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ ብዙ ለማየት አብቅቶናል፡፡ ማን የእግዚአብሔር ካህን ማን የተቃራኒው እንደሆነ፤ ማን ኃይማኖተኛ ማን ፖለቲክኛ፤ ማን አማኝ ማን ከሀዲ እንደሆነ ለማየት ታድለን ነበር፡፡ መንገዳቸውን በሃይማኖታቸው ያስተካከሉ ባዕታቸውን የዘጉ ግዜያቸውን፣ አገልግሎታቸውን ለአምላካቸው ብቻ የሰጡ ብጹአን መነኮሳት አባቶች የመኖራቸውን ያህል ባንፃሩ ደግሞ በስተርጅና ዕድሜያቸው የሃይማኖት አባትነታቸውን እንዳሮጌ ካባ በመጣል ጭልጥ ብለው ወደ ፖለቲካው መስመር መግባታቸው የጴጥሮስነት ሃላፊነታቸውን በመርገጥ ዋናፀሐፊው  ሲኖዶሱን  የግላቸው ሥልጣን ማእከል፣ የፖለቲከኞች ቁማር መጫወጫ ማድረጋቸው በምዕመን ዘንድ አልተወደደላቸውም፡፡ እግዚአብሔርስ ቢሆን ቤቱን ቄሳር ሲጓደድበት ይወዳል ብላችሁ ነው?

 

ወንድማችሁ ኃይለገብርኤል ታደገ

Posted in Uncategorized | 1 Comment